በወቅታዊው የእግርኳስ ሁኔታ “ተስፋ ቆርጫለው” ያለው ደቡብ ፖሊስ ሊፈርስ ይሆን ?

ባሳለፍነው የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ቻምፒዮን በመሆን ከስምንት ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ መመለስ የቻለው ደቡብ ፖሊስ በዘንድሮው የውድድር ዓመት በመጀመሪያው ዙር ያሳየውን ደካማ አቋም በሁለተኛው ዙር በእጅጉ አሻሽሎ ቢቀርብም በ29ኛው ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 1-1 ከተለያየ በኋላ ተመልሶ መውረዱን አረጋግጧል፡፡

ሆኖም ክለቡ የወረደበት መንገድ “ሕገ-ወጥ” መሆኑን በመጥቀስ ቅሬታውን ያቀረበ ሲሆን ፌዴሬሽኑ በህግ አግባብ ክለቡ የጠየቀውን ጥያቄ በአግባቡ የማይመልስ ከሆነ ለመፍረስ እንደሚገደድ የስፖርት ክለቡ ፕሬዝዳንት ኮማንደር ዳንኤል ገዛኸኝ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ክለባቸው የእግርኳስ ህግጋት ተገዢ ሆኖ ሲወዳደር እንደቆየ ገልፀው ወልዋሎ ከ ሽረ ያደረጉት ጨዋታ ላይ የነበረው ክስተት አሳፋሪ ነው ብለዋል። ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን ተመልክቶ ትክክለኛውን እርምጃ ካልወሰደም ከተመሰረተ 17 ዓመታት ያስቆጠረው ክለብ ሊፈርስ እንደሚችል ገልፀዋል።

ኮማንደር ዳንኤል ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጡት ቃል ይህንን ይመስላል:-

“ቅሬታችን በጣም ብዙ ነው። ከመጀመሪያው ጀምሮ የነበረውን አሁን መናገር ከባድ ነው። ወደ ውድድር ከገባን ጀምሮ እኛ በንፁህ ህሊና የእግር ኳሱን ሕግ አክብረን ነው እየተወዳደርን ያለነው። በሜዳችን በቅርቡ የገጠመንን እናንተ ታውቃላችሁ። እኛን ከውድድር ውጪ ለማድረግ ሌሎች አካላትም ሲሰሩ ነበር። በርካታ እጅግ በጣም አሳዛኝ ነገሮች ተደርገዋል። በተለይ ወልዋሎ ከሽረ የነበረው ጨዋታ መመልከት ይቻላል። እኛ እኮ ከቡና ጋር ስንጫወት ቡናን በገንዘብ ለመግዛት መሞከር እንችል ነበር። ሆኖም እንዲህ ዓይነት ተግባር ስራችን ስላልሆነ ለዚህ የተዘጋጀ ህሊና የለንም። በጨዋታው የምንችለውን ነገር አድርገን ነጥብ ተጋርተን ወጥተናል። መቆየት ካለብን በሊጉ እንቆያለን፤ ካልቻልን እንወርዳለን።

” መቐለ ላይ የተሰራው ስራ ህገ-ወጥ እና አሳፋሪ ነው። እኛ ብዙ መረጃ አለን። ያ ሁሉ ካሜራ፣ ያ ሁሉ አወዳዳሪ አካል፣ ዳኞች እና ይህ ሁሉ ባለሙያ ታዲያ ለምን ሄደ ? የእኛ ጥያቄ ከወልዋሎ ነጥብ ተነጥቋል፣ አሰልጣኙ ዮሐንስ ሳህሌም በሜዳ ላይ አልነበረም፤ የወልዋሎ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች በሰዓቱ ያለቅሱ ነበር። እኚህ ሰዎች ወደ የሀገራቸው ሲሄዱ ምን አይነት አመለካከት ይኖራቸዋል። ሦስት ካሜራ ነበር ተብሏል፤ የዳኛ ሪፖርት ይኖራል። ስለዚህ በህግ አግባብ መወሰን አለበት። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ከፌዴሬሽኑ ጋር ያለንን ግንኙነት እናቋርጣለን።

” በተፈፀመው ሕገ ወጥነቱ የተረጋገጠ አሳዛኝ ተግባር ላይ ፌዴሬሽኑ ትክክለኛውን ውሳኔ እንዲወስን ግፊት እናደርጋለን። ይህ ካልሆነ ደግሞ እግርኳሱን ትተን ወደ ዋናው ፀጥታ የማስከበር ተግባራችን እንመለሳለን። የእኛ ዋናው እና ትልቁ ተልዕኳችን ፀጥታ ማስከበር ነው። ሆኖም ጎን ለጎን ስፖርቱን ለማሳደግ እና ለስፖርቱ ባለን ፍቅር የማንም ዕገዛ ሳይኖረን ነው ክለቡን እዚህ ማድረስ የቻልነው። የሚሰሩ ስራዎች አግባብነት የሌላቸው እየሆኑ ስለመጡ ግን እዚህ ጋር ለመቆም እንገደዳለን። እኔ በግሌ 17 ዓመት በዚህ ክለብ ቆይቻለሁ። እንደ ልጄም የማየው ክለብ ነው፡፡ እኔ በስራዬ ተስፋ ባልቆርጥም በእንዲህ ዓይነት ህገ ወጥ ስራዎች ነጥብን በጉልበት ለማግኘት እየተሞከረ በመሆኑ የበላይ አመራሮች ተስፋ እየቆረጡ መጥተዋል። ፌዴሬሽኑም ስፖርቱ እንዲያድግ አይፈልግም የሚል ስሜት ስላላቸው ከአቅማችን በላይ እየሆነ መጥቷል።

የመጨረሻውን የሊግ ጨዋታ እናደርጋለን፤ በውሳኔው ዙርያ ተስፋን አንቆርጥም። ግን የሚሰሩ ስራዎች ግልፅ ካልሆኑ እና ትክክለኛው ውሳኔ ካልተሰጠ ይህን ትልቅ ክለብ ዳግም የማናየው ሊሆን ይችላል። ያድጋል ብለን ተስፋ በማናደርገው ስፖርት ላይ በዚህ ሁኔታ መቀጠል አንችልም” ፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡