ኢትዮጵያን ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶሴሽን የመጀመርያ ጉባዔውን አካሄደ

ከተመሠረተ አጭር ጊዜ የሆነው ኢትዮጵያን ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶሴሽን በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ዛሬ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ከአባላቶቹ ጋር ረጅም ሰዓት የፈጀ ውይይት በማድረግ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

ከታሰበበት ከአንድ ሰዓት በላይ ዘግይቶ 04:30 በጀመረው ስብሰባ የማኅበሩ መስራች እና ሰብሳቢ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ማኅበሩ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆንም የባለሙያውን መብት ለማስከበር ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ መቆየቱን በመግለፅ ዓላማውን ለተሳታፊዎች በዝርዝር አስረድተዋል። በመቀጠልም ” እናንተ አሉ የምትሉትን ችግሮች በግልፅ ተነጋግረን አንድ አቅጣጫ መያዝ ይገባናል።” በማለት የሚሰማቸውን ስሜት እንዲገልፁ መድረኩን ለተሳታፊ አባላት ክፍት አድርገዋል።

ተሳታፊዎቹ ” እስከዛሬ ብዙ በደሎች ሲደርሱብን መብታችንን የሚያስከብርልን ማኅበር ባለመኖሩ ብዙ ችግሮችን በዝምታ አልፈናል። ከፌዴሬሽኑም ሆነ ከክለቦች ጋር ለመካሰስ አቅም አልነበረንም። አሁን ግን ለእኛ የሚቆረቆር ማኅበር በመቋቋሙ ደስተኞች ነን። ይህን ኃላፊነት በመውሰድ እንዲቋቋም ላደረጋቹ የቀድሞ ተጫዋቾች እና አሁን እየተጫወታቹ ለምትገኙ መስራቾች ከፍተኛ ምስጋና እናቀርባለን።” ያሉት ተሳታፊዎቹ አሉ የሚሉትን ችግሮችን በዝርዝር ተናግረዋል። በዋናነት ካነሷቸው ነጥቦች መካከል፡-

* ከዚህ ቀደም እኛን ሳያማክሩ የፊርማ ገንዘብ ይቅር በደሞዝ ይሁን መባሉን በዝምታ ማለፋችን ከፍተኛ ችግር ፈጥሮብናል።

* የውል ዘመናችን ሳይጠናቀቅ ክለቦች እንደፈለጉ እያሰናብቱን መብታችንን ማስከበር አቅቶን ለከፋ ጉዳት ተዳርገናል።

* ባላጠፋነው ጥፋት ፌዴሬሽኑም ሆነ ክለቦች በማን አለብኝነት ከፍተኛ የሆነ ቅጣት ሲጥሉብን በዝምታ ነው ያለፍነው።

* ጉዳት አስተናግደን በውሉ መሠረት የህክምና ወጪውን ክለቡ እንዲሸፍን ደንቡ ቢያስገድድም ዞር ብሎ የሚመለከተን ባለመኖሩ ለተጨማሪ ወጪ ተዳርገናል።

* በምንጫወትባቸው አንዳንድ ክለቦች የአራት እና የሁለት ወር ደሞዝ እየተከፈለን ባለመሆኑ ችግር ውስጥ ገብተናል። እነዚህን እና መሰል ችግሮችን በትዕግስት እያለፍን ባለንበት በአሁኑ ወቅት እኛ ባልተካፈልንበትና ያለ እኛ ይሁንታ ፍቃድ የተጫዋች የደሞዝ ጣሪ ከ50 ሺህ በር በላይ እንዳይሆን መወሰን ተገቢ አይደለም ብለዋል። ይህን ውሳኔም የማንቀበለው እና የማናምንበት በመሆኑ እኛ ለማኅበሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን። እናንተ በምትችሉት ሁሉ መብታችንን ለማስከበር ስሩ የሚሉት ይገኙባቸዋል።

የማኅበሩ አመራሮችም የተወሰነውን ውሳኔ ከዚህ ጉባዔ አስቀድሞ በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ሲቃወሙት እንደቆዩ ገልፀው በጋራ በተጠናከረ ሁኔታ አቋማቸውን መግለፅ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በማስከተል በህግ ባለሙያ አማካኝነት የተወሰነው ውሳኔ ከህግ አንፃር ያለውን ሁኔታ ለተሳታፊዎቹ ማብራሪያ የተሰጣቸው ሲሆን በመጨረሻም አንድ ደረጃ ላይ መድረስ እንዳለባቸው የህግ ባለሙያው በሰጣቸው ምክረ ሀሳብ መነሻነት ይህ ውሳኔ ባለሙያውን የማይወክል፣ የማይመጥን መሆኑን የጋራ በሆነ የአቋም መግለጫ በመግለፅ ጉባዔው 10:00 ላይ ተጠናቋል።

የአቋም መግለጫው ዝርዝር ሁኔታ ነገ አልያም ከነገ ወድያ ማኅበሩ ለሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት እንዲሁም ለመገናኛ ብዙኀን ይፋ የሚያደርገው መሆኑን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡