መሰቦ ሲሚንቶ የደደቢት ንብረትነት ትናንት ተረከበ

በፋይናንስ እጥረት ሲቸገሩ የቆዩት ሰማያዊዎቹ ችግራቸውን የሚቀርፍላቸውን የባለቤት ሽግግር አድርገዋል።

ባለፉት ዓመታት በፕሪምየር ሊጉ ጥሩ ስም ከነበራቸው እና ጠንካራ ቡድኖች አንዱ የነበረው እና ባለፈው የውድድር ዓመት ከፋይናንስ ጋር በተያያዘ ከባድ የውድድር ዓመት አሳልፎ ከሊጉ የወረደው ደደቢት በቀጣይ ዓመት በመሰቦ ሴሜንት ባለቤትነት እና በተሻለ አሰራር እንደሚመለስ ተገልጿል። ፋብሪካው ቡድኑ ወደ ቀድሞ ዝናው እንዲመለስ በፋይናንስ ረገድ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉንም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በ1989 በታዳጊ ፕሮጀክት መልክ የተመሰረተው ደደቢት በሒደት የክለብ ቁመና ይዞ በውድድሮች ላይ በመሳተፍ በ2002 ወደ ፕሪምየር ሊግ ካደገ በኋላ በቀጣዮቹ ዓመታት ከፍተኛ ወጪ ከሚያወጡ ቡድኖች ቀዳሚ የነበረ ሲሆን የሊጉን ዋንጫ ካነሳ በኋላ በፋይናንስ እጥረት ሲቸገር ቆይቷል። ቡድኑን በገንዘብ እንዲደግፍ ተቋቁሞ የነበረው ደራ (ደደቢት ራዕይ) ትሬዲንግም የሚያመነጨው ገቢ የክለቡ ወጪዎችን ለመሸፈን በቂ እንዳልነበር ክለቡ ባለፈው ዓመት በሰጠው መግለጫ ላይ መግለፁ ይታወሳል።

ደደቢትን በባለቤትነት የተረከበው መሰቦ ሲሚንቶ ከክለቡ ጋር ቁርኝት ያለው ኩባንያ ነው። ባለፉት ሦስት የውድድር ዘመናትም የክለቡ የማልያ ስፖንሰር እንደነበር የሚታወስ ነው።

መቀመጫቸውን ወደ መቐለ ካዞሩ በኃላ ለከተማው ታዳጊዎች ዕድል መስጠት አልቻሉም በሚል ባለፈው ዓመት በርካታ ተቃውሞዎች የደረሳቸው ሰማያዊዎቹ በቀጣይ ለከተማው ታዳጊ ተጫዋቾች የተሻለ ዕድል ለመስጠት እንዳሰቡ ሲታወቅ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠርም ከጫፍ ደርሰዋል።

በተያያዘ ዜና ደደቢትን በበላቤትነት የተረከበው መሰቦ ሴሜንት በቀጣይ ቀናት ለሚድያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡