የደቡብ ካስቴል ዋንጫ በዚህ ወር አጋማሽ ይጀመራል

በየዓመቱ የፕሪምየር ሊግ ክለቦችን የሚያሳትፈው የደቡብ ሪጅናል ካስቴል ዋንጫ ዘንድሮ ከሁለት ሳምንት በኋላ መካሄድ ይጀምራል።

ለሰባተኛ ጊዜ የሚደረገው ውድድሩ አስር ክለቦችን ተሳታፊ በማድረግ ከጥቅምት 15 ጀምሮ እንደሚደረግ በቅርቡ በተደረገ ጠቅላላ ጉባዔ የደቡብ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት አቶ ደመላሽ ይትባረክ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ትላንት በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በተደረገ ስብሰባም ውድድሩን ካለፉት ዓመታት አንፃር በተሻለ ይዘት ለማዘጋጀትም ቅድመ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ጨምረው ገልጸዋል፡፡ 

የክልሉን ክለቦች ሀዋሳ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ወላይታ ድቻን ከፕሪምየር ሊጉ የሚይዝ ሲሆን በከፍተኛ ሊግ እንዲወዳደሩ የተወሰነባቸው ደቡብ ፖሊስ እና አርባምንጭ ከተማንም ተሳታፊ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተጋባዥነት ደግሞ ጅማ አባጅፋር፣ አዳማ ከተማ እና በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እንደሚሳተፍ እየተነገረ ያለው ሰበታ ከተማን በውድድሩ ተካፋይ ለማድረግ ጥሪ እንዳቀረቡ የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ወልደሚካኤል መስቀሌ ተናግረዋል፡፡

በቢጂአይ ኢትዮጵያ ስፖንሰር አድራጊነት ለመጨረሻ ጊዜ በካስቴል ስያሜ የሚደረገው ይህ ውድድር ከውድድርነቱ ባለፈ ክለቦችን የሚያቀራርቡ ሥራዎች ለመስራት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑ ሲገለፅ በሆሳዕና ከተማ ለማድረግ ታስቦ የነበረው ይህ ውድድር ሜዳው በእድሳት ላይ በመሆኑ በሀላባ ቁሊቶ ከተማ ለማድረግ መወሰኑን የፅህፈት ቤት ሀላፊው ለሶከር ኢትዮጵያ ጠቁመዋል፡፡

በተያያዘም ለአምስተኛ ጊዜ በከፍተኛ ሊግ ክለቦች የሚደረገው የካስቴል ውድድር ውድድር በኅዳር ወር አጋማሽ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ