ወልቂጤ ከተማ አጥቂ ሲያስፈርም አምስት ተጫዋቾችን አሳድጓል

በሀዋሳ የቅድመ ውድድር ዝግጅት በማድረግ ላይ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ ሳዲቅ ሴቾን ሲያስፈርም አምስት ወጣቶችንም ከተስፋ ቡድኑ አሳድጓል፡፡

በመስመር እና በፊት አጥቂነት መጫወት የሚችለው ሳዲቅ ሴቾ ከዚህ ቀደም ወዳሳለፈበት ወልቂጤ በድጋሚ ተመልሶ ፊርማውን አኑሯል፡፡ ሼር ኢትዮጵያን ለቆ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ተጉዞ ከፕሪምየር ሊግ ጋር የተዋወቀው አጥቂው ቡናማዎቹን ከለቀቀ በኋላ በሀዋሳ ከተማ እና አምና ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ቆይታን አድርጎ ወልቂጤ ከተማን ተቀላቅሏል፡፡

ወልቂጤ ከተማዎች ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች በተጨማሪ ወጣት ተስፈኛ ተጫዋቾችን ከከፍተኛ ሊጉ ከማምጣታቸው ባለፈም አምስት የተስፋ ቡድኑ ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን ያሳደጉ ሲሆን በዚህ መሠረት ዳንኤል መቅጫ (የተከላካይ አማካይ)፣ ቸርነት ተስፋዬ (ተከላካይ) ቴፐኒ ፍቃደ (አጥቂ)፣ አድናን ፈይሰል (አማካይ)፣ ቢኒያም አብዮት (ግብ ጠባቂ) በቢጫ ቴሴራ በአዲስ አዳጊው ቡድን ውስጥ መካተት የቻሉ ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡

ወልቂጤ ከተማዎች በቀጣዩ ሳምንት በሀዋሳ ሲያደርጉ የነበሩትን ዝግጅት አጠናቀው በአዲስ አበባ ከተማ ሲቲ ካፕ ለመሳተፍ ወደ ስፍራው እንደሚያመሩም ይጠበቃል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ