ሪፖርት| ወልዋሎዎች በአስደናቂ አጀማመራቸው ቀጥለዋል

ቢጫ ለባሾቹ ስሑል ሽረን 3-0 በማሸነፍ ነጥባቸው ወደ ዘጠኝ ከፍ አድርገዋል።

በጨዋታው ወልዋሎዎች ከባለፈው ሳምንት አሰላለፋቸው ሄኖክ መርሹ እና ሰመረ ሃፍታይን በጁንያስ ናንጂቦ እና ኢታሙና ኬይሙኔ ተክተው ሲገቡ ስሑል ሽረዎች በበኩላቸው በሲዳማ ቡና ከተሸነፈው ስብስባቸው በረከት ተሰማ ፣ ክብሮም ብርሃነ ፣ ዓብዱሰላም አማን ፣ ሙሉዓለም ረጋሳ እና ሳሊፍ ፎፋና በማስወጣት በዮናስ ግርማይ ፣ አዳም ማሳላቺ ፣ ክፍሎም ገብረህይወት ፣ መድሃኔ ብርኃኔ እና ሃብታሙ ሽዋለም ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ብዙም ሳቢ ያልነበረው እና በርካታ የግብ ዕድሎች ባልተፈጠሩበት የመጀመርያው አጋማሽ ወልዋሎዎች ለአጥቂዎች በሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት ሲሞክሩ ስሑል ሽረዎች በተለመደው የመስመር አጨዋወት ጎል ለማግኘት ጥረት አድርገዋል።

ኢታሙና ኬይሙኔ ከመስመር አሻግሯት ምንተስኖት አሎ ወጥቶ ባዳናት ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት ወልዋሎች በተጠቀሰው አጨዋወት በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል። ከነዚህም ሳሙኤል ዮሐንስ አሻግሯት ኢታሙና ኬይሙኔ ሳይጠቀምባት የቀረው ሙከራ ትጠቀሳለች። በአስራ ስድስተኛው ደቂቃም ገናናው ረጋሳ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ሳሙኤል ዮሐንስ ከቅጣት ምት ያሻማትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። 

በጨዋታው በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ያገኟቸውን ጥቂት አጋጣሚዎች በአግባቡ የተጠቀሙት ወልዋሎዎች በሃያ ስምንተኛው ደቂቃ የጎል ልዩነቱ ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል። ጁንያስ ናንጂቡ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ከተከላካዮች አምልጦ በመቆጣጠር ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝንቶ ነበር ያስቆጠረው።

በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ አጀማመር የነበራቸው እና በኳስ ቁጥጥር ብልጫም የተሻሉ የነበሩት ስሑል ሽረዎች ምንም እንኳ በርካታ ንፁህ የግብ ዕድሎች ባይፈጥሩም በተወሰኑ አጋጣሚዎች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ከነዚህም ያሳር ሙገርዋ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መቷት ለጥቂት የወጣችው ኳስ እና ዲድየ ሌብሬ በሁለት አጋጣሚዎች ያገኛቸው ወርቃማ ዕድሎች ይጠቀሳሉ።

በቁጥር ትንሽ የግብ ሙከራዎች እና በፍጥነቱ ከመጀመርያው አጋማሽ የወረደ እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይህ ነው የሚባል ትልቅ የግብ ዕድል ያልተፈጠረበት ነበር። ሆኖም በወልዋሎ በኩል ጁንያስ ናንጂቡ ከምንተስኖት አሎ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው በጥሩ ብቃት ያዳነው ሙከራ እና ካርሎስ ዳምጠው ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቶ ምንተስኖት አሎ ያዳነው ሙከራ ይጠቀሳሉ። በሃምሳ አምስተኛው ደቂቃም ጁንያስ ናንጂቡ ከራምኬል ሎክ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ግብ በማስቆጠር በጨዋታው ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሶስተኛ ግቡን አስቆጥሯል።         

በስሑል ሽረ በኩል ሳሊፍ ፎፋና በሳጥን ውስጥ ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ እና ዓብዱለጢፍ መሐመድ  ከኃይልአብ ኃይለሥላሴ የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ ያደረጋት ሙከራ የውጤቱን ልዩነት ለማጥበብ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

ጨዋታው በዚ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ወልዋሎዎች ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን ሲያስመዘግቡ ስሑል ሽረዎች በተከታታይ ሁለተኛ ጨዋታ ሽንፈት አስተናግደዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ