የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 1-2 ሲዳማ ቡና 

ዛሬ በተካሄደው የሦስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲዳማ ቡና ጅማ አባ ጅፋርን 2-1 በሆነ ውጤት ካሸነፈ በኋላ አሰልጣኞች የሰጡት አሰተያየት የሚከተለው ቸው።

“አቅደን የመጣነው ሦስት ነጥብ ነበር፤ አሳክተናል” የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ጥሩ ነበር። መልካም እንቅስቃሴም ተመልክተንበታል። በእኛ በኩል ከእረፍት በፊት አልፎ አልፎ ተከላካዮቻችን የሚፈጥሩት ስህተት እኛን አደጋ ውስጥ ይከተን ነበር። ከእረፍት በኋላ አስተካክለናል፤ ያም ቢሆን ብዙ የግብ ዕድሎችን ፈጥረን አልተጠቀምንም። ሆኖም ከሜዳ ውጭ እንደመጫወታችን ማሸነፍ እንዳለብን አቅደን የመጣነው ሦስት ነጥብ ማሳካት ነበር፤ አሳክተናል።

ከማጥቃት ወደ መከላከል ሽግግሩ ክፍተት

ትክክል ነው ይህ በዛሬው ጨዋታ ላይ ይታይብን የነበረ ክፍተታችን ነው። አጥቅተን ወደ መከላከሉ ስንመጣ ክፍተቶች ይታያሉ። ይህ ደግሞ ከትኩረት የመውጣት ችግር ነው። ይህ ደግሞ ከተጫዋቾቼ ጋር ቁጭ ብለን በንግግር የሚስተካከል ስለሆነ አርመን በቀጣይ እንመጣለን።

” ስለ ቀጣዩ ነገር ከማውራት እቆጠባለሁ” የጅማ አባ ጅፋር አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው

ስለ ጨዋታው

በተጫዋቾቼ የዛሬ እንቅስቃሴ ኮርቻለው፤ ከዚህ ውጭ ስለ ዳኝነቱ ብዙ ማለት አልፈልግም። ቡድኔ ግን ብዙ አማራጭ ያሉት በወጣት የተገነባ ቡድን ነው። ብዙ የግብ ዕድሎች ፈጥሯል፣ በጣም አጥቅተን ነው የተጫወትነው። ብንሸነፍም በቡድኔ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ማንንም አልወቅስም።

ከሜዳ ውጭ ያለው የቡድኑ ችግር በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ቡድኑ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ

ይሄ ምንም የሚያጠያይቅ ነገር አይደለም፤ እየተመለከታችሁት ነው። ስለ እርሱ መናገር አልፈልግም። በአሁን ሰዓት ወጣት ተጫዋቾች አሉ፤ እነርሱን እያጫወትኩ ነው። ስለ ቀጣዩ ነገር ከማውራት እቆጠባለው፤ ለሌላው ትቼዋለው። ብቻ በአባሉኝ ልጆች ደስተኛ ነኝ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: