የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የዛሬ ውሎ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ሁሉም ጨዋታዎች ዛሴ ተከናውነዋል። የዕለቱን ውሎም እንዲህ አጠናቅረነዋል።

ምድብ ሀ

04:00 ኢ/ወ/ስ አካዳሚን ከ ወላይታ ድቻ ያገናኘው ጨዋታ በእንግዳው ቡድን ወላይታ ዱቻ 2–1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ከመስመር ከሚነሱ ብሎም ከመዐዘን ምት ከሚሻገሩ ኳሶች የሚፈጥሩት አደጋ ከባድ የሆኑት ወላይታ ድቻዎች በአጥቂያቸው ቢንያም ብርሃኑ አማካኝነት ሁለት ግልፅ የማግባት አጋጣሚዎች አግኝተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

በአካዳሚ በኩል ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም የዱቻ ተጫዋቾችን የፍጥነት፣ የተክለ ሰውነት እና የጉልበት ብልጫን መቆጣጠር አቅቷቸው ኳሶቻቸው ቶሎ ቶሎ ይቆራረጡ ነበር። ያም ቢሆን በ37ኛው ደቂቃ በጥሩ መንገድ ወደ ወላይታ ድቻ የግብ ክልል የገቡት አካዳሚዎች ዓምና ከ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ መልካም የሚባል የውድድር ጊዜ ያሳለፈው ኤርምያስ ጌታቸው ጎል አስቆጥሮ ቀዳሚ መሆን ችለዋል።

ከእረፍት መልሰ ወደ ጎል በመድረስ ከፍተኛ ብልጫ የወሰዱት ወላይታዎች አንድ የግብ አግዳሚ ከመለሰባቸው ጥሩ ሙከራ በኃላ በ53ኛው ደቂቃ የአካዳሚው ግብጠባቂ ላይ ጥፋት ተሰርቶበት መሬት ወድቆ በቀጠለው ጨዋታ የድቻው አጥቂ መልካሙ ቦጌ በግንባሩ በመግጨት የአቻነት ጎል አስቆጥሯል። በዚህችም ጎል ሒደት ላይ የአካዳሚ አሰልጣኝ እና ተጫዋቾቻቸው ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

ብዙም ሳይቆይ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር በፍጥነት የተንቀሳቀሱት ወላይታ ድቻዎች ከመሐል ሜዳ የተጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ ተመስገን ብርሀን ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል ድቻዎች መሪ አደርጓል።

ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ አካባቢ የአቻነት ጎል ፍለጋ አካዳሚዎች ጥረት አድርገዋል በተለይ ፈይሳ ከቅጣት ምት የተሻገረለት ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት አቻ መሆን የሚችሉበት መልካም የሚባል አጋጣሚ ነበር ። ጨዋታውም በወላይታ ድቻ 2-1 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።

08:00 በአዲስ አበባ ስታድየም በተካሄደው የኢትዮጵያ ቡና እና የጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት እንግዶቹ ጥሩነሽ ዲባባዎች በዳንኤል ታምሩ ቀዳሚ ቢሆንም በኢትዮጵያ ቡና በኩል በየነ ባንጃ የአቻነት ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው 1–1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በመቀጠል 10:00 በተካሄደው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የመከላከያ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር እና ድራማዊ ትዕይንት አስተናግዶ በሦስት አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በመጀመርያው አጋማሽ እንደወሰዱት ብልጫ ጎል ማስቆጠር የሚገባቸው ፈረሰኞቹ በዳግማዊ አርዓያ ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከነበራቸው ጨዋታ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ወደ ሜዳ የገቡት መከላከያዎች ወደ ጎል በመድረስ ሁለት ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አግኝተው በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ አድጎ ዘንድሮ ጊዮርጊስን የተቀላቀለው ተስፋኛው ግብጠባቂ ዳዊት በኃይሉ በአስደናቂ ሁኔታ አምክኖባቸዋል። የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በያብስራ ሙልጌታ ግሩም የቅጣት ጎል መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል። ብዙም ሳይቆይ ዳግማዊ አርዓያ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከመጀመርያው አጋማሽ መከላከያዎች ተሽለው ሲታዩት ፈረሰኞቹ በሦስት ጎል መምራታቸው በፈጠረባቸው ከልክ ያለፈ በራስ መተማመን ዋጋ አስከፍሏቸዋል። የመስመር ተከላካዮ ፉአድ ሙዘሚል ከርቀት ባስቆጠራት አስደናቂ ጎል የተነቃቁት መከላከያዎች ወደ መጨረሻው ደቂቃ ተሾመ በላቸው አከታትሎ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ከሦስት ለዜሮ መመራት ተነሥተው ሦስት አቻ መሆን ችለዋል። መከላከያ አቻ ከመሆናቸው አስቀድሞ ፈረሰኞቹ በዳግማዊ፣ በፀጋዬ መላኩ እና ተቀይሮ በገባው አቤል አዱኛ አማካኝነት ያልተጠቀሙባቸው ኳሶች የበለጠ ቡድኑን ዋጋ ያስከፈሉ ሲሆን በዋናው ቡድን ያደገው ቴዎድሮስ ገ/እግዚአብሔር ከዕለቱ ዳኛ ጋር በፈጠረው አላስፈላጊ ሰጣ ገባ በሁለት ቢጫ በቀይ ካር ከሜዳ ተወግዷል። ጨዋታውም በዚህ መልክ 3–3 አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በሌላ የምድቡ ጨዋታ ይርጋለም ላይ ሀዋሳን የገጠመው ሲዳማ ቡና 1-0 አሸንፏል። ይስሀቅ ከኖ የብኛዋ ጎል ባለቤትም ነው።

ምድብ ለ

ወደ ሱሉልታ ያመራው ፋሲል ከነማ 2-1 ማሸነፍ ችሏል። ፋሲል ማሩ እና አቤል ገረመው የዐፄዎቹን ጎሎች ሲያስቆጥሩ አሚር መሐመድ የሱሉልታን አስቆጥሯል።

አሰላ ላይ አሰላ ኅብረት ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2-2 አቻ ተለያይተዋል። ባለፈው ሳምንት አራፊ በመሆናቸው ምክንያት በዚህ ሳምንት የመጀመርያ ጨዋታቸውን ላደረጉት አሰላዎች ሐይማኖት ግርማ ሁለቱንም ጎሎች ሲያስቆጥር ፀጋ ደርቤ እና ጃዱ ሸምሴ የኤሌክትሪክን ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ባለፈው ሳምንት በሜዳው በመድን ሽንፈት የገጠመው አዳማ ከተማ ከሜዳው ውጪ ሀላባ ከተማን 1-0 መርታት ችሏል። አቤል ደንቡ ደግሞ የብቸኛዋ ጎል ባለቤት ነው።

አአ ከተማ ወልቂጤ ከተማን 3-1 የረታበት ጨዋታም የዚህ ሳምንት መርሐ ግብር አካል ነበር። ሙከሪም ምዕራብ፣ ምንተስኖት ዘካርያስ እና ኪያር መሐመድ የአአ ከተማን ጎሎች ሲያስቆጥሩ አብዱልፈታ ከሊፋ የወልቂጤን አስቆጥሯል።

© ሶከር ኢትዮጵያ