ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ንግድ ባንክ ተከታዩን አሸንፎ ልዩነቱን ሲያሰፋ ሀዋሳ እና መቐለም አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች (11ኛ ሳምንት) ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ ንግድ ባንክ እና ሀዋሳ ከተማ በሜዳቸው፤ መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ ከሜዳ ውጪ አሸንፈዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-1 ጌዴኦ ዲላ

(በዳንኤል መስፍን)

ንገሠድ ባንክ በፍፁም የበላይነት ጌዲዮ ዲላን በማሸነፍ ወደ ዋንጫ የሚያደርገውን ግስጋሴ አጠናክሮ ቀጥሏል። 09:00 ሲኤምሲ በሚገኘው የንግድ ባንክ ሜዳ በተካሄደው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ የእንቅስቃሴ ብልጫ ወስደው በተደጋጋሚ ከመስመር ከሚነሱ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር የተንቀሳቀሱት ባለሜዳዎቹ ንግድ ባንኮች ጎል አያስቆጥሩ እንጂ ጫና ለመፍጠራቸው ማሳያ በመጀመርያው አስር ደቂቃ ውስጥ ከ3 በላይ የማዕዘን ምት ማግኘታቸው ነበር።

ንግድ ባንኮች ጎል ለማስቆጠር የነበራቸው ጥረት ቀጠሎ በ17 ደቂቃ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው የነበረ ቢሆንም ረሂማ ዘርጋው ሳትጠቀምበት ቀርታ የግቡ ቋሚ መልሶባታል። ብዙም ሳይቆይ ትግስት ያደታ ከመስመር ያሻገረችላትን ሁሌም በጥሩ ብቃቷ የምትገኘው ብርቱካን ገ/ክርስቶስ ኳሱን በደረቷ አብርዳ የመታችውና የጎሉ አግዳሚ የመለሰባት በንግድ ባንክ በኩል ሌላ ለጎል የቀረበ ሙከራ ነበር።
በመጀመርያው አጋማሽ በጥሩ መከላከል በራሳቸው ሜዳ በዝተው ረድዔት አስረሳኸኝን ትኩረት ያደረገው የእንግዶቹ የጌዲዮ ዲላ አጨዋወት አልፎ አልፎ ወደ ጎል ለመድረስ ከሚደረግ ጥረት ውጭ ብዙም የተሳካ አልነበረም። በአንድ አጋጣሚ 34ኛው ደቂቃ ረድየት አስረሳኸኝ ከርቀት አክራ የመታችውና ግብጠባቂዋ ንግስቲ ወደ ውጭ ያወጣችባት ሙከራ ተጠቃሽ የሚሆን ነው።

በሁለተኛው አጋማሽ ኳሱን ተቆጣጥረው በሁሉም የሜዳ ክፍል በጥሩ ሁኔታ አደራጅተው ጎል ፍለጋ በተደጋጋሚ ወደ ጌዲዮ የግብ ክልል የደረሱት ንግድ ባንኮች በ59ኛው ደቂቃ የመስመር ተከላካይ ብዙዓየሁ ታደሰ ወደ ሳጥኑ ሰብራ በመግባት አመቻችታ ያቀበለቻትን ረሂማ ዘርጋው በቀላሉ ኳሱን ደገፍ አድርጋ ባስቆጠረችው የመጀመርያውን ጎል መምራት ጀምረዋል። ከደቂቃዎች በኃላ ሌላ ተጨማሪ የጎል መጠናቸውን ማስፋት የሚችሉበትን አጋጣሚ ሽታዬ ሲሳይ አግኝታ ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ይሄም ቢሆንም 72ኛው ደቂቃ በግምት ከ30 ሜትር ርቀት የተገኘውን ቅጣት ምት ገነሜ ወርቁ በቀጥታ ወደ ጎል መታ አስገራሚ ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችላለች።

በእንቅስቃሴ ብዙም ሜዳ ውስጥ ያልነበሩት ዲላዎችን ከሽንፈት ያልታደገች ጎል በ89ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ ተቀይራ የገባችው ትዝታ ፈጠነ በግንባሯ ገጭታ በማስቆጠር ጨዋታው በባለሜዳዎቹ የበላይነት 2-1 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀዋሳ ከተማ 2-1 አዳማ ከተማ

(በቴዎድሮስ ታከለ)

ሌላው በሳምንቱ ተጠባቂ የነበረውና ፋታ የለሽ እንቅስቃሴ በታየበት የሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ በባለሜዳዎቹ ን 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ 9:00 ሲል በጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱ ቡድኖች በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እና በቅብብል የተዋጣላቸው ቢሆንም ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ሳጥን ተጠግቶ ተፅኖ በመፍጠር የተሻሉ ነበሩ። አዳማ ከተማዎች ደግሞ በተሻጋሪ ኳሶች ወደ ሀዋሳ ግብ ክልል በማድረስ ግብ ለማግኘት ጥረትን ቢያደርጉም የሀዋሳ የተከላካይ ክፍል ጠጣርነት ለቡድኑ አዳጋች ሆኖ ታይቷል፡፡ በግብ ሙከራ ረገድ አዳማ ከተማዎች ቀዳሚዎች ናቸው። የምስራች ላቀው በግራ አቅጣጫ የተገኘን ቅጣት ምት ተጠቅማ ወደ ግብ ስትመታው ግብ ጠባቂዋ አባይነሽ ኤርቀሎ ይዛባታለች፡፡

በመሐል ሜዳ ላይ ከወትሮ በተለየ አቀራረብ በዛ ብለው ወደ አጥቂዎች ኳስን በማሻገር የተዋጣላቸው ሀዋሳ ከተማዎች በአጥቂዎቻቸው ያለመረጋጋት ኳስን እያገኙ በቀላሉ ሲያመክኑ አስተውለናል፡፡ በተለይ ምስር ኢብራሂም በሁለት አጋጣሚዎች ለግብ ቀርባ የነበረች ቢሆንም በችኮላ መጠቀም ያልቻለችበት ተጠቃሽ ነበር፡፡ ሆኖም ተሳክቶላቸው 14ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ከማዕዘን ምት ዓይናለም አደራ በረጅሙ ወደ ግብ ስታሻማ ሳራ ኬዲ በደረቷ አቀዝቅዛ ዳግም ለዓይናለም ሰታት ዓይናለም መሬት ለመሬት ወደ ሳጥን ስትልከው ተከላካይዋ ቅድስት ዘለቀ ከመረብ አሳርፋ ሀዋሳ ቀዳሚ አድርጋለች፡፡

ከግቧ በኃላ የሀዋሳን የተከላካይ ክፍል ለማለፍ ሲቸገሩ የነበሩት ሴናፍ ዋቁማ እና ምርቃት ፈለቀ ምንም እንኳን አላፈናፍን ቢሏቸውም ከቆሙ ኳሶች በተለይ ምርቃት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችላለች፡፡ በዚህም ሂደት ተሳክቶላት አሳዳጊ ክለቧ ላይ ግብ አስቆጥራለች፡፡ 24ኛው ደቂቃ የሀዋሳዋ ተከላካይ ትዝታ ኃይለሚካኤል ከግብ ክልሉ ውጪ በግራ በኩል በሴናፍ ዋቁማ ላይ የሰራችውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ምርቃት ፈለቀ በቀጥታ መትታ የዓባይነሽ ኤርቄሎ የአያያዝ ስህተት ታክሎበት አዳማን 1ለ1 አድርጋለች፡፡

ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ ሀዋሳዎች በፈጣን ቅብብል ወደ አዳማ ግብ ክልል ደርሰው ነፃነት መና ለግብ የቀረበ ሙከራን ብታደርግም መስከረም ካንኮ ከግቡ መስመር በግሩም ሁኔታ አውጥታዋለች፡፡

ከእረፍት መልስ በተመሳሳይ ለተመልካች ዕይታ ሳቢ ሆኖ የቀጠለው ጨዋታ የአዳማ ከተማ የመልሶ ማጥቃት የባለሜዳው ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ ግብ ጋር ለመድረስ የሚያርጉት የቅብብል ሒደት ሁነኛ መገለጫዎች ነበሩ፡፡ 51ኛው ደቂቃ የምስራች ላቀው በግራ በኩል በግል ጥረቷ ኳስን እየገፋች ወደ ሳጥን ገብታ ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረችሁ ሴናፍ መስጠት ሲገባት በራሷ ለማስቆጠር ጥረት ማድረጓ የተገኘውን መልካም አጋጣሚ አምክናዋለች፡፡ ከዚህች ሙከራ በኃላ በሀዋሳ በተወሰነ መልኩ ለመበለጥ የተገደዱት ቻምፒዮኖቹ የተበታተነ የመከላከል መንገዳቸው ለነጭ ለባሾቹ የማጥቃት ስትራቴጂ የተመቹ ሆነውላቸዋል። 78ኛው ደቂቃም ለሽንፈት ያበቃቸውን ግብ አስተናግደዋል፡፡ በፈጣን የቅብብል መልሶ ማጥቃት ወደ አዳማ ግብ ክልል የደረሰችሁ ኳስ ነፃነት መታ በፍጥነት በቅድስት ቴካ ተቀይራ የገባችሁ ዙፋን ደፈርሻ ከሳጥን ውጪ መትታ በእምወድሽ ይርጋሸዋ መረብ ላይ አሳርፋለች፡፡

አዳማ ከተማዎች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች የሀዋሳን የማስጠበቅ መንገድ ቀልብሶ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። በተለይ በጭማሪ ደቂቃ እፀገነት ብዙነህ ከቀኝ በኩል በረጅሙ ወደ ግብ ስታሻማ ሴናፍ ዋቁማ በግንባር ለማግኘት ስትታትር ለጥቂት ያመለጣት በመጨረሻው ደቂቃ ቡድኑን አንድ ነጥብ ለማግኘት የሚያስችል የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ በመቅረቱ ጨዋታው በሀዋሳ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

አአ ስታዲየም ላይ አዲስ አበባ ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ ያደረጉት ጨዋታ በእንግዶቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ለመቐለ የድል ጎሎቹን ሳሮን ሰመረ ስታስቆጥር ለአዲስ አበባ ከተማ አስናቀች ትቤሶ አስቆጥራለች።

የሊጉ አንደኛ ዙር የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ሐሙስ እና እሁድ ሲደረጉ ነገ አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከ መከላከያ፤ ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከ አቃቂ ቃሊቲ ይጫወታሉ።

© ሶከር ኢትዮጵያ