የከፍተኛ ሊግ 1ኛ ዙር የመሪ ክለቦች ዳሰሳ – ነቀምቴ ከተማ

የ2012 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያው ዙርን በመሪነት የጨረሱ ቡድኖችን መዳሰሳችንን ቀጥለን በምድብ ለ ቀዳሚ ሆኖ ያጠናቀቀው ነቀምቴ ከተማን ተመልክተነዋል።

የመጀመሪያ ዙር ጉዞ

በአሰልጣኝ ቾምቤ ገብረሕይወት የሚመራውና ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ተጠናክሮ የቀረበው ነቀምቴ በዘንድሮ ውድድር ዓመት ከ11 ጨዋታ 24 ነጥብ በመሰብሰብ ጠንካራ ቡድኖች የተሰባሰቡበት የምድብ ለን በአንደኝነት አጠናቋል።

በክረምቱ በአዲስ ፎርማት ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንደሚቀላቀሉ ከተወሰነላቸው ቡድኖች መካከል አንዱ የነበሩት ነቀምቴዎች ለሊጉ የሚሆን ዝግጅት መጀመራቸው ኋላ ላይ ፎርማቱ ውድቅ ሆኖ በከፍተኛ ሊጉ ሲቀጥሉ ጥሩ የውድድር ጊዜ እንዲያሳልፉ እንደረዳቸው ይታመናል።

በከፍተኛ ሊግ አወዳዳሪ አካል ከዓምናው ምድብ ሐ በማውጣት ወደ ምድብ ለ ተዘዋውሮ ውድድሩን ያደረገው ነቀምቴ በሜዳው ተጋጣሚዎችን በሰፋ የግብ ልዩነት የሚያሸንፍ ሲሆን ከሜዳው ውጪ ደግሞ ቢያንስ ግብ ሳይቆጠርበት አቻ የሚወጣ ጠንካራ ቡድን ሆኖ ታይቷል። ቡድኑ በመጨረሻ ካደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ውስጥም በአራቱ አሸንፎ አንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ መለያየቱ ምን ያህል ድንቅ አቋም ላይ እንደሚገኝ ማሳያ ነው።

ነቀምቴ ከተማ በአንደኛው ዙር በቁጥሮች

ደረጃ – 1ኛ
ተጫወተ – 11
አሸነፈ – 7
አቻ – 3
ተሸነፈ – 1
ነጥብ – 24

ጎል
አስቆጠረ – 16
ተቆጠረበት – 3

የቡድኑ አቀራረብ

አሰልጣኝ ቾንቤ ገብረሕይወት ዘንድሮ ሁለት መልክ ያለው ነቀምቴ ከተማን ይዘው ብቅ ብለዋል። በሜዳቸው ሲጫወቱ ኳስን ተቋጣጥሮ መጫወት የሚችሉ አማካዮች በማካተት በ3-5-2 አደራደር ተጋጣሚያቸው የጎል ክልል ቶሎ ቶሎ የሚደርሱ ሲሆን ተደጋጋሚ ጫና በመፍጠርም ጎሎች ለማስቆጠር ይጥራሉ። በተቃራኒው ከሜዳቸው ውጪ ለጥንቃቄ ቅድሚያ በመስጠት እና አሰላለፋቸውን ወደ 4-5-1 በመቀየር መከላከል ላይ የሚያተኩሩ ሲሆን ረጃጅም ኳሶችም በአመዛኙ ይጠቀማሉ። በዚህም ለተጋጣሚ ክፍተት ባለመስጠት ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዞ የሚወጣ ቡድን ሆኗል።

ቡድኑ በፊት አጥቂነት ተቀዳሚ ምርጫቸው ከሆነው የቀድሞ ተጫዋቻቸውና ዘንድሮ የተመለሰው ኢብሳ በፍቃዱ እንዲሁም ቴዎድሮስ መንገሻ ሲሆኑ በተለይም ከሜዳቸው ውጭ ላለው አጫወታቸው ይበልጥ የሚስፈልጋቸው ኢብሳ የአየር ላይ ኳሶችን በአግባቡ የሚጠቀምም ነው። ሆኖም ጎሎችን በማስቆጠሩ ረገድ መሻሻል የሚገባው ክፍል ነው።

ነቀምት ከተማ ኳስን በአማካይ ክፍሉ ኳስ ተቆጣጥረው መጫወት የሚችሉ፣ ጎሎች የሚያስቆጥሩ እንዲሁም ለከፍተኛ ሊጉ እጅግ አስፈላጊ ለሆነው የአካል ንክኪ አስፈላጊ የሆኑ ተጫዋቾትን ያሰባሰበ ሲሆን ለቡድኑ ጥንካሬም ዋንኛ ምክንያቶች ናቸው።

በሊጉ እጅጉን ጠንካራ የሚባል የተከላካይ ክፍል ማዋቀር የቻለው ነቀምቴ ሦስት ግቦችን ብቻ ማስተናገዱ የተከላካዩን ክፍል ጥንካሬ የሚገልፅ ነው።

ጠንካራ ጎን

ቡድኑ በሥነ ልቦና ረገድ ያለው ጥንካሬ ከማንኛውም ቡድን የተሻለ ነው ማለት ይቻላል። በምድቡ ጠንካራ ቡድኖች ቢኖሩም ነጥቦች በቀላሉ ሲጥሉ የሚታይ ሲሆን ነቀምቴ በተቃራኒው ድል ለማስመዝገብ የሚያሳዩት ተጋድሎ የሚጠቀስ ነው። በዚህም በሜዳው ቢያንስ በሁለት የጎል ልዩነት በማሸነፍ ሲወጣ ከሜዳው ውጪ ደግሞ በጠንካራ መከላአል ቢያንስ አንድ ነጥብ ለማስመዝገብ ይተጋል።

በመከላከሉ ረገድ ያለው ጥንካሬ ዋንኛ የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው። በ11 ጨዋታ ሦስት ጎሎች ብቻ የተቆጠረበት ቡድኑ የኋላ እፍሉ ጥንካሬ እንዳለ ሆኖ አማካዮቹ ለተከላካይ ክፍሉ የሚሰጠው ሽፋን በቀላሉ ጎል እንዳይቆጠርበት አድርጎታል።

በዘንድሮ ውድድር ዓመት የዐምና ኮከብ ግብ አግቢያቸው ዳንኤል ዳዊትን ያጡት ነቀምቴዎች ሁነኛ ጎል አስቆጣሪ ባያገኙም ከበርካታ ተጫዋቾች ጎሎች ማግኘታቸው እንደሌሎች ቡድኖች አንድ ተጫዋቾች ላይ የማግባት ኃላፊነት እንዳይንጠለጠል አድርጎታል።

ደካማ ጎኖች

ከሜዳ ውጭ ያለው የቡድኑ ውጤት እጅግ ዝቅተኛ ነው። ቡድኑ ከሜዳ ውጪ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች አንድ ጎል እና አንድ ድል ብቻ ያስመዘገበ ሲሆን አንድ ሽንፈት ብቻ ቢያስተናግድም ለማሸነፍ የሚያደርገው ጥረት ዝቅተኛ ነው።

የጎል ማስቆጠር ችግር ሌላው ደካማ ጎኑ ነው። በአጠቃላይ ካስቆጠረው 16 ጎሎች አስራ አምስቱ በሜዳው ያስቆጠራቸው መሆኑ ሲታይ ቡድኑ ከሜዳው ውጪ እና በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ጎል የማስቆጠር ችግሮች እንደሚታዩበት አመላካች ነው።

ለሁለተኛ ዙር ምን ይጠበቃል?

ለሁለተኛው ዙር በተጫዋቾች ዝውውር ላይ ይሳተፈል ተብሎ የሚጠበቀው ነቀምቴ ከሜዳ ውጭ ላለበት ጫና ይረዳው ዘንድ የአጥቂውን ቁጥር በማብዛት ይበልጥ ጫናዋችን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

©ሶከር ኢትዮጵያ