የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 1-0 አዳማ ከተማ

በ16ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አዳማን በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም የጋበዘው ፋሲል ከነማ 1-0 በሆነ ውጤት ጨዋታውን ካጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።


“ጨዋታውን ማሸነፋችን የሥራችን ውጤት ነው” ሥዩም ከበደ (ፋሲል ከነማ)

ጨዋታው እንዴት ነበር?

በሁለታችንም በኩል የነበረው ነገር ጥሩ ነበር። እኛ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ስለምንገኝ እያንዳንዱን ጨዋታ በጥንቃቄ ነው የምናደርገው። ዛሬም በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረን ነገር ጥሩ ነበር። ነገር ግን በመጀመሪያው ዙር የነበሩብን የመዘናጋት እና ትናንሽ ስህተቶች ተጨዋቾቻችንን ወደ ኋላ ጎትቶብን ነበር። ከዚህ በተጨማሪም አዳማዎች ጋር የነበረው ነገር ጥሩ ነበር። በአጠቃላይ ግን ጨዋታውን ማሸነፋችን የስራችንም ውጤት አለበት እና ደስተኞች ነን።

በመጀመርያ አሰላለፍ ስለተጠቀሟቸው ተጨዋቾች?

አዲስ ተጨዋች አልተጠቀምንም። ሙሉ ለሙሉ የነበሩት ተጨዋቾች ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ አብረውን የነበሩ ናቸው። ቋሚ የመሆን እድል ስላላገኙ ነው እንጂ አብረውን የነበሩ ናቸው። ኪሩቤልም የበለጠ የራስ መተማመን ኖሮት እንዲጫወት ነው ያደረግነው። በተጨማሪም ግብ ጠባቂው ቴዎድሮስ እድል ሳያገኝ ቆይቶ ነበር። ነገር ግን የሳማኬ በጊዜው አለመገኘትን ተከትሎ ዛሬ እድሉን በአግባቡ ተጠቅሟል። ሳማኬም ሲመለስ ይህ ግብ ጠባቂ እስካልተበላሸበት ጊዜ ድረስ ቁጭ ብሎ ይጠብቃል ማለት ነው። ቴዎድሮስ ላይ እያየን ያለነው ነገር በጎ ነገሮችን ነው።

የቡድኑ ጠንካራ እና ደካማ ጎን?

በዛሬው ጨዋታ የነበረን ጠንካራ ጎን ጨዋታው ሲጀምር የነበረው ነገር ነው። በተለይ ለማጥቃት የምናደርገው ነገር በጣም መልካም ነበር። ነገር ግን የያዝነውን ነጥብ የማስጠበቅ ነገር ላይ ክፍተቶች ነበሩብን። ይህ ነገር ከባለፉት ጨዋታዎች መሻሻሎችን ቢያሳይም በሜዳ ላይ ክፍተቶችን ስንፈጥር ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ያገኘነውን እድልም ሳንጠቀም ወጥተናል። በአጠቃላይ ግን የነበረን መነሳሳት ጥሩ ነበር።

“እኛ ዛሬ ዳኛ ነው የገጠምነው” ደጉ ዱባም (አዳማ ከተማ – ምክትል አሰልጣኝ)

ጨዋታውን እንዴት አገኘኸው?

በመጀመሪያ አስበን የመጣነው 3 ነጥብ ይዞ ለመሄድ ነበር። ነገር ግን ዳኛው ያሰብነውን እንዳናሳካ አድርጎናል። ትክክለኛ ውሳኔዎች ሜዳ ላይ ሲወሰኑ አልነበረም። ይህ ደግሞ ተጨዋቾቻችን ተረጋግተው እንዳይጫወቱ አድርጎታል። በአጠቃላይ በዳኝነት ስህተት ምክንያት ጭቅጭቆች የበዙበት ጨዋታ ነበር። እኛ ዛሬ ዳኛን ነው የገጠምነው። በእንቅስቃሴ ደረጃ ግን በሁለተኛው አጋማሽ እኛ ተጭነን ተጫውተናል።

ስለቡድኑ እቅድ እና ስለተጨዋች አመራረጥ?

እነሱ በሦስት አጥቂ ስለሚጫወቱ ጥንቃቄዎችን በማድረግ እና በመስመር ተከላካዮቻችን ጥቃቶችን ለማድረግ ነበር አስበት የገባነው። ነገር ግን በጉዳት ምክንያት ገና በጊዜ የተጨዋች ለውጥ እንድናደርግ ሆኗል። ይህ የተጨዋች ለውጥም ብዙ ነገሮችን አበላሽቶብናል። በተለይ በሱሌማን በኩል ነበር ለማጥቃት ያሰብነው ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቷል። በአጠቃላይ እኛ አጋጣሚዎች የመጠቀም ችግር ነበረብን።

በሁለተኛው አጋማሽ የነበረው የበላይነት ከምን የመጣ ነበር?

በሁለተኛው አጋማሽ እኛ ጠንካራ ነበርን። ግብ ስለተቆጠረብን ያለንን አቅም ተጠቅመን ለመንቀሳቀስ ሞክረናል። የግብ ማግባት እድሎችንም ፈጥረን ነበር። ነገር ግን እነዛን የግን ማግባት አጋጣሚዎች ሳንጠቀምበት ቀርተናል።

በሁለተኛ ዙር ከአዳማ ምን ይጠበቅ?

በሁለተኛ ዙር የተሻለ ነገር ይኖረናል ብለን እናስባለን። እኛ ከ1-3ኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው። ነገር ግን ይህ የሚሆነው አስተዳደራዊ ችግሮቻችን ከተቀረፉ ነው። ይህ ቡድን በደንብ አቅም ያለው ስለሆነ ከ1-3 ሆነ መጨረስ በትክክል ይችላል። ግን እንደገለፅኩት የእኛ የበላይ ሰዎች ቡድኑ ውስጥ ያለውን የደሞዝ ችግር በቶሎ መፍታት ከቻሉ ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ