የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 1-0 ጅማ አባ ጅፋር

በ16ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ጅማ አባጅፋርን በሜዳው 1-0 ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ደጋፊዎቻችን ደስ ብሏቸው ከሜዳ ስለወጡ በጣም ደስ ብሎኛል” ፋሲል ተካልኝ (ባህር ዳር ከተማ)

ጨዋታው እንዴት ነበር?

በጨዋታው ኳሱን እራሳችን ጋር አቆይተን ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል ለመድረስ ሞክረናል። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የማጥቃት ፍጥነታችን በጣም ጥሩ ነበር። ነገር ግን በሁለተኛው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ትንሽ አፈግፍገን ነበር። በአጠቃላይ ግን ማሸነፋችን ተገቢ ነው።

በሁለተኛው አጋማሽ ስለተበለጡበት ምክንያት?

ጨዋታውን በልጠውናል ማለት አይቻልም። እርግጥ ነው እኛ ትንሽ አፈግፍገናል። ነገር ግን ወደ ጎል ቶሎ ቶሎ በመድረሱም ረገድ በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ነበርን። እንደተባለው ግን በዚህ አጋማሽ አንደ መጀመሪያው አጋማሽ አልተንቀሳቀስንም።

ቡድኑ በርከት ያሉ እድሎችን ስላመከነበት ምክንያት?

መጀመሪያ ደስ ያለኝ ነገር እነዛን የጎል እድሎች መፍጠር መቻላችን ነው። የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ በተደጋጋሚ ለመድረስ ሞክረናል። ነገር ግን ለማመን የሚከብዱ ኳሶችን አምክነናል። በተለይ ከውሳኔ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ስህተቶች ነበሩብን። አንዳንድ ጊዜ የቀንም ጉዳይ ነው። አንድ ቀን ሁለት እና ሶስት ጎል ልታገባ ትችላለክ አንዳንዴ ደግሞ አይሳካም። ሆነም ቀረ ይህንን ነገር እኛ በዛሬው ጨዋታ ያሳየነው ደካማ ጎን አድርገን እንወስደዋለን። አጥቂያችን ስንታየሁ ብዙ ኳስ አምክኗል። ነገር ግን ወጣት ስለሆነ ይማራል። እንደ አሰልጣኝ ነገ ብሔራዊ ቡድን ይደርሳል ብዬ የምጠብቀው ተጨዋች ነው።

ሳላምላክ ስለተሰለፈበት የተለየ ቦታ?

ዛሬ ለሳላምላክ የተለየ ሚና ሰጥቼዋለሁ። ተጨዋቹ የመስመር አጥቂ ሆኖ የመጫወት ልምድ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ። በዚህ ዓመት ግን በዚህ ቦታ ላይ ተጫውቶ አያውቅም። ይህ ደግሞ የሆነው ከተጫዋቾች ጉዳት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው።

“ወደ እረፍት ልንወጣ ስንል በፈጠርነው የጥንቃቄ ጉድለት ያስተናገድናት ጎል ዋጋ አስከፍላናለች” ጳውሎስ ጌታቸው (ጅማ አባጅፋር)

ጨዋታውን እንዴት አገኘኸው?

ጨዋታው ጥሩ ጨዋታ ነበር። ብዙ የመጠቃቃት ነገር የታየበት ነው። እረፍት ልንወጣ ስንል በፈጠርነው የጥንቃቄ ጉድለት ያስተናገድናት ጎል ዋጋ አስከፍላናለች። ብዙ ልጆችን ይዘን ሳንመጣ ነው ወደ ሜዳ የገባነው። በአጠቃላይ ግን የነበረው ነገር የሚያስከፋ አልነበረም። ከዚህ በኋላ የፊታችን ዓርብ ላለው ጨዋታ መዘጋጀት እንጀምራለን።

ተጨዋቾችህ የምትፈልገውን ተግብረውልሃል?

ዛሬ ካለቦታቸው ያጫወትናቸው ተጨዋቾች ነበሩ። እንደ አጠቃላይ ተጨዋቾቼ ጥሩ ነገር ለማሳየት ሞክረዋል። በተለይ መስመር ላይ የነበሩት ተጨዋቾች የባህር ዳርን የመስመር ላይ ጥቃት ለማቆም በጥሩ ሁኔታ ተንቀሳቅሰዋል። ያገኘናቸውንም አጋጣሚዎች የግቡ ቋሚም ሆነ ሃሪሰን የተመለሱበት እድል አስቆጪ ነበር። ነጥብ መጋራት መበረብን፤ ነገር ግን አልተሳካልንም።

የቀድሞ ክለብህ ጠንካራ ጎን?

የባህር ዳር ጠንካራ ጎን ደጋፊው ነው። በጣም ምርጥ ሀብት አለው። ተጨዋቾቹም የሚነሳሱት በእነዚህ ደጋፊዎች ነው።

ስለተደረገለት መልካም አቀባበል?

ጥሩ መስራት መልካም ነው። ጥሩ መስራት ለራስ ነው። ሁልጊዜ በሙያክ ታማኝ ከሆንክ ታሪክ ያስታውስሃል። ባህር ዳር እያለሁ እንደ ግርማ ዲሳሳ አይነት ተጨዋቾችን ማውጣቴን ሳይ ትልቅ ደስታ ነው የሚሰማኝ። ዛሬ ያየሁኋቸው ተጨዋቾች በአብዛኞቹ የራሴ ስለሆኑ ኩራቴ ነው።

©ሶከር ኢትዮጵያ

error: