ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛው ሳምንት ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና እጅግ ቀዝቃዛ በነበረው ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ተለያይተዋል።

ሀዋሳ ከተማዎች ባለፈው ሳምንት በድሬዳዋ ሽንፈት ካስተናገደው ቡድን ውስጥ በአራት ተጫዋች ላይ ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ሀብቴ ከድር በቢሊንጋ ኢኖህ ፣ ላውረንስ ላርቴን በወንድማገኝ ማዕረግ ፣ ተስፋዬ መላኩን በአክሊሉ ተፈራ ፣ ሄኖክ አየለን በብርሀኑ በቀለ ለውጠዋል፡፡ በተመሳሳይ ሀዲያ ሆሳዕናዎች በአራት ተጫዋቾች ላይ ለውጥ በማድረግ በቅርቡ ያስፈረሟቸውን ተጫዋቾች በሙሉ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አካተው ጀምረዋል፡፡ ፀጋሰው ድማሙን በመድሀኔ ብርሀኔ ፣ በረከት ወልደዮሃንስን በቢኒያም ሲራጅ ፣ ሱራፌል ዳንኤልን በተስፋዬ አለባቸው እንዲሁም ቢስማርክ ኦፖንግን በሳሊፍ ፎፋና ተክተዋል፡፡

የስራ ቀን እንደመሆኑ ብዙም ተመልካች ተገኝቶ መከታተል ባልቻለው እና ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ ሳይቸገሩ በመሩት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አስራ አምስቱ ደቂቃዎች የቡድኖቹን የአጨዋወት መንገድ ለመረዳት ከመሞከር ይልቅ ተጫዋቾች ኳስን ለመንጠቅ በሚያደርጉት ጥረት ተደጋጋሚ ጥፋቶች የታዩበት ገፅታ ነበረው፡፡ ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከይሁን እንዳሻው የሚነሱ ረጃጅም ኳሶችን ወደ ፊት በመጣል ጥቃት ለመሰንዘር ቢጥሩም ከፊት የተሰለፉ ተጫዋቾች በስሎ ያለመገኘት ለሀዋሳ ተከላካዮች የመከላከል ሂደቱን አቅሎላቸዋል።

ሀዋሳዎች በከፈቱት መልሶ ማጥቃት 10ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ሄኖክ ድልቢ በረጅሙ ሲያሻግር ብሩክ በየነ በግንባር ገጭቶ ካመከነ ሦስት ደቂቃዎች ብቻ እንደተቆጠሩ ግብ አስቆጥረዋል፡፡ 13ኛው ደቂቃ ላይ አክሊሉ ተፈራ ከቀኝ በኩል በረጅሙ ሲያሻግር መስፍን ታፈሰ በሚገባ ተቆጣጥሮ እና የሀዲያ ሆሳዕና ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ ወደ ሳጥን ከተጠጋ በኃላ አክርሮ ሲመታ ኳሷ የግቡን ቋሚ ሁለቴ ከነካች በኃላ ከመረብ ተዋህዳ ሀዋሳ ከተማን መሪ አድርጋለች።

ሆሳዕናዎች ልክ እንደ ሀዋሳ በእንቅስቃሴ ረገድ ደከም ብለው ቢታዩም ቀዳዳን እየፈለጉ ከርቀት በመምታት ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል፡፡ ለዚህም ማሳያ ተከላካዩ አዩብ በቀታ ከርቀት መትቶ ግብ ጠባቂው ባሊንጋ በቀላሉ የያዘበት አጋጣሚ በዋናነት የሚጠቀስ ሙከራ ሲሆን 30ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ይሁን እንዳሻው መሀል ለመሀል አሾልኮ ወደ ሀዋሳ ግብ ክልል የላካትን ኳስ ቢስማርክ አፒያ እና ሳሊፍ ፎፋና ለማግኘት ሲሮጡ ተጋጭተው የቆሙ ሲሆን ከሁለት አንዱ ኳሷን ቀድሞ አግኝቷት ቢሆን ኖሮ ነብሮቹን አቻ የምታደርግ አስቆጪ ዕድል ነበረች፡፡

ከዚህ ሙከራ በኃላ ኃይቆቹ በመስፍን ታፈሰ ላይ ያነጣጠሩ የማጥቂያ አማራጮችን ለመፍጠር ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡ አጥቂው በተደጋጋሚ በግሉ ወደ ሳጥን ሰብሮ በመግባት ሙከራዎችን ሲያደርግ አስተውለናል፡፡ መደበኛው ደቂቃ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ብቻ እየቀረ ሀድያ ሆሳዕናዎች የሀዋሳን የመከላከል ስህተት ተጠቅመው አቻ ለመሆን በቅተዋል፡፡ 45ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት ይሁን እንዳሻው በረጅሙ ወደ ግብ ሲያሻማ አዩብ በቀታ አግኝቶ በቀጥታ ወደ ግብ ሲመታ ቢሊንጋ ኢኖህ እንደምንም ከመለሳት በኃላ የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች ዝንጉነት ታክሎበት አፈወርቅ ኃይሉ በፍጥነት ደርሶ አየር ላይ እንዳለች በግንባር በመግጨት አስቆጥሮ ውጤቱን ወደ 1-1 ለውጦታል።

ከዕረፍት መልስ ሆሳዕናዎች የአጥቂ ክፍላቸውን ጨምረው ግብ አስቆጥሮ ለማሸነፍ ጥረት ቢያደርጉም ደከም ብሎ የቀረበላቸውን የሀዋሳ ከተማን ክፍተት ለመጠቀም ያደረጉት ጥረት እና ውሳኔ እጅግ ደካማ በመሆኑ ያለሙትን ማሳካት ሲሳናቸው ተመልክተናል፡፡ ረጃጅም ኳስ በመጠቀም ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ መድረስ ቢችሉም ደካማው የመጨረሻ የውሳኔ አሰጣጣቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ በተለይ በጨዋታው በግሉ ለአጥቂዎች ኳስ ለመመገብ ያልሰሰተው ይሁን እንዳሻው በርካታ አጋጣሚዎችን ከፊት ለተሰለፉት ተጫዋቾች መፍጠር ቢችልም ወደ ግብነት የሚለውጣቸውን ሁነኛ ሰው አላገኙም፡፡ በ61ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ይሁን በረጅሙ ሲያሻግር አዩብ በግባር ገጭቶ ያመከናት እና በመልሶ ማጥቃት በረጅሙ ይሁን በአግባቡ የሰጣቸውን ቢስማርክ አፒያ እና ሳሊፍ ፎፋና ኳሷን ለማግኘት በፈጠሩት ትርምስ ቤሊንጋ ደርሶ አድኖባቸዋል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ ተቀዛቅዘው የታዩት ሀዋሳዎች አክሊሉ ተፈራ በቀኝ በኩል ለሄኖክ ሰጥቶት አማካዩ ወደ ግብ መትቶ ኦቬር ኦቮኖ ከያዘበት እና የተሻ ግዛው ካለመረጋጋት በችኮላ ከሳታት ኳስ ውጪ ወደ ሀድያ የግብ ክልል ከመድረስ ተቆጥበዋል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩት ይሁን እንዳሻው ብልጠቱን ተጠቅሞ ተቀይሮ ለገባው ሱራፌል ጌታቸው አሳልፎለት አማካዩም ወደ ሳጥን እየገፋ ገብቶ ከግብ ጠባቂው ቢሊንጋ ጋር አንድ ለአንድ ከተገናኘ በኃላ የመታት ኳስ የግብ ጠባቂው ጥረት ታክሎባት በላይኛው የግቡ ብረት ስር ያለፈችበት የመጨረሻ ደቂቃ አጋጣሚ ሆሳዕናዎችን አሸናፊ ለማድረግ ተቃርባ ነበር።

ከጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቅ በኋላ የሀዋሳ ከተማው ተጫዋች እና ዛሬ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጦ የነበረው ተስፋዬ መላኩ ከደጋፊዎች ጋር የፈጠረው ሰጣገባ ትኩረት የሚስብ አጋጣሚ ነበር፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ