የአበበ ቢቂላ የጤና ስፖርት ማኅበር የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

በንግድ፣ በሚዲያ እና በሌሎች መስኮች እየተሳተፉ የሚገኙ እንዲሁም የቀድሞ ታዋቂ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች የተቋቋመው የአበበ ቢቂላ የጤና ስፖርት ማኅበር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት የሚያግዝ የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ምስረታውን 2006 ያደረገው ይህ ማኅበር በአውሮፓ፣ በአሜሪካ የኢትዮጵያዊያን የስፖርት ፌስቲቫሎች ለተከታታይ ዓመታት በስኬት በማዘጋጀት ይታወቃል። የአበበ ቢቂላ የጤና ስፖርት ማኅበር በአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ለስፖርት ለሁሉም በሚያዘጋጃቸው የጤና ቡድኖች ውድድሮች ላይም በተደጋጋሚ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

ከዚህ ቀደም በተለያዩ ማኅበራዊ ተግባራት ላይ ድጋፍ በማድረግ የሚታወቀው የአበበ ቢቂላ የጤና ቡድን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያቀረበውን የድጋፍ ጥሪ በመቀበል ግምቱ ከሁለት መቶ ሺህ ብር በላይ የሆነ የምግብ እና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ በዛሬው ዕለት በከተማው አስተዳደር ቅጥር ግቢ በመገኘት ድጋፍ አድርጓል፡፡ በቀጣይነት አባላቱን በማሰባሰብ ቀጣይ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ