የሴቶች ገፅ | ከመጀመሪያ ሴት ተጫዋቾች አንዷ እና ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በለጥሽ ገብረማርያም…

በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ላለፉት ሀምሳ ዓመታት ያህል ዕድገቱ ፈጣን እንዲሆን የነበራት ድርሻ ቀላል አይደለም። ከመጀመሪያ የክለብ ተጫዋቾች አንዷ ከመሆን አንስቶ እስከ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት በግል ጥረቷ ደርሳ አገልግላለች። በርካታ ውጣ ውረዶችን ዓይታ ለሴቶች እግር ኳስ ዕድገት ጠበቃ በመሆን ምንም ካልነበረበት ዛሬ ወደነበረበት በማድረሱ ረገድ ሚናዋ ቀላል የሚባል አይደለም። በዛሬው የሴቶች ገፅ አምዳችንም ስኬታማዋ ተጫዋች እና አሰልጣኝ በለጥሽ ገብረማርያምን የህይወት ጉዞ ይዘን ቀርበናል።

ለሴቶች እግር ኳስ ትኩረት መንሳት ብቻ ሳይሆን እንስት ሆኖ ሜዳ ላይ ኳስን ማንከባለል እንደውግዘት በሚቆጠርበት ዘመን እሷ ግን ያን ሁሉ አሸንፋ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ሴት ልጅ እግር ኳስን መጫወት እንድትችል ፈር ቀዳጅ በመሆን ቀዳሚዋ ናት ፤ በለጥሽ ገብረማርያም። ትውልድ እና እድገቷ አዲስ አበባ ባቡር ጣቢያ ውስጥ ነው፡፡ በአካባቢው ማኅበረሰብ በ1960ዎቹ እግርኳስ መጫወት የተለመደ በመሆኑ በወቅቱ ያ ቦታ በቁጥር በርካታ እግር ኳስ ተጫዋቾችን አፍርቷል፡፡ በለጥሽም ዕድሜዋ እያደገ ሲመጣ ከተማሪነቷ ጎን ለጎን ባቡር ጣቢያ የሚገኘው የእግር ኳስ ሜዳ ላይ በርከት ያሉ ክለቦችም ሆኑ ታዳጊዎች ልምምድ ሲያደርጉ የያኔዋ ተማሪ ከትምህርቷ ቀረት እያለች የቡድኖቹን ልምምድ ትመለከታለች። በተደጋጋሚ የሚጫወቱትን በትኩረት መመልከቷ ግን በይበልጥ እየወደደችው እንድትመጣ አደረጋት። ወደ ተጫዋችነት ከመግባቷ አስቀድሞ ኳስ ሲጫወቱ ከሜዳ ውስጥ ወደ ውጪ ኳሷ ስትወጣ ከጓደኞቿ ጋር እያመላለሰች ፍቅሯን በደንብ ማሳደግ ጀመረች። ግን በቤተሰቧ ውስጥ በተለይ አባቷ በትምህቷ ብቻ እንጂ ሴት ልጅ ወደ ሜዳ ወጥታ መጫወትን ስለማይደግፉ ተፅዕኖ ቢኖርባትም ሁለት ወንድሞቿ እግር ኳስ ተጫዋች መሆናቸው እና ለእሷም ሲያደርጉላት የነበረው ድጋፍ እጅጉን የላቀ በመሆኑ ብዙ ፈተናዎችን ብትጋፈጥም የወንድሞቿ እርዳታ ግን ህልሟን ዕውን አደርጎላታል።

“ሁለት ወንድሞቼ እግር ኳስን ይጫወቱ ነበር። የእነሱንም ሆነ የሌሎች ቡድን ተጫዋቾችን ልምምድ አያለሁ። ታዳጊ ልጆችም በባቡር ሜዳ ሲጫወቱ በደንብ እመለከታለሁ። ከዛ በኃላ ግን እግር ኳስ ውስጤ ገባ። ትንሽ ዕድሜዬ እየጨመረ ሲመጣ እኔም መጫወትን ጀመርኩ። ከወንድሞቼ ውጪ ሴት እኔ ብቻ ስለሆንኩ ቤተሰቤም መጫወቴን አይደግፉም ነበር። ከዛ ሌላ አካባቢ ያሉ ልጆችን ይዘን አንድ ቡድን መመስረት እንዳለብን ስናስብ እኔንም ወንድሞቼ ስላዩ እነሱ ጣልቃ ገቡ። ከዛ የእግር ኳስ ዝንባሌ ያላቸውን ልጆች አሰባሰብንና እኛ ሰፈር ላይ መጫወት ጀመርን። ዝም ብለን እየተከፋፈለን ሰውን ለማለማመድ ያህል በክለብ ሳይሆን ለሁለት እየተከፈለን መለማመድ ጀመርን። በርከት ስንል አብዛኛዎቻችን የምድር ባቡር ሰፈር ልጆች ስለሆንን የአብዛኞቻችን ቤተሰቦቻች እዛው ስለሚሰሩ ምድር ባቡር እንዲይዘን ጠየቅን።” በማለት ወደ እግር ኳስ ተጫዋችነት ለመግባት ስለከፈለችው መስዋዕትነት እና አዲስ አበባ ምድር ላይ የመጀመሪያውን ክለብ ለመመስረት ስለሄደችበት እልህ አስጨራሽ ጉዞ ትገልፃለች፡፡

ክለብ ተቋቁሞ ማየት ውጥኗ ስለነበር የምድር ባቡርን ጠይቃ ድርጅቱ እሺታውን አልነፈጋትም። ባቡር ትራንስፖርት እና ምግብ ድሬዳዋ ካለ ቡድን ጋር ጨዋታ ካላቸሁ ደግሞ ማረፊያ እንዲሁም መለያ ሰጥቷቸው ምድር ባቡር የሴቶች ክለብ ተብሎ 1964 ላይ የመጀመሪያው የሴት ክለብ ተመሠረተ። በለጥሽም ለዚህ ክለብ መመስረት ግንባር ቀደሙን ቦታ ትወስዳለች፡፡ “ሁለቱ ወንድሞቼ አስፋው ገብረማርያም እና ተፈራ ገብረማርያም ኳስ ተጫዋች መሆናቸው ጠቅሞኛል ፤ ተፈራ ገብረማርያም ኒያላ ይጫወት ነበር። ካቆመ በኃላም በቦርድ አባልነት ሰርቷል። አስፋው ደግሞ የምድር ባቡር ተጫዋች ነበር። ስፖርተኛ ስለነበሩ የእነሱ ተጫዋች መሆን ለእኛ ክለብ መመስረት አስተዋጽኦ ነበረው። ምድር ባቡር ከያዘን በኃላ ጥሩ ሆነልኝ። ወንድሜም እዛ ነው የሚሠራው አባቴም ምድር ባቡር ሰራተኛ ነበር። የብዙዎቻችን ቤተሰቦች የምድር ባቡር ሰራተኞች ነበሩ። ምድር ባቡር መጫወት ከሁለት አንፃር ነው፤ አንደኛ የምንበላበትና የምናድርበት ነው። እሱም ስሙን ለማስጠራት የመጀመሪያው ክለብ ነው፡፡ ስለዚህ ሌሎች ሴቶችን ማንቃት አለብን በሚል ተነሳን።”

እግርኳስን ሴት ልጅ መጫወት አለባት በሚል ተነስታ ለስኬት ያበቃችው በለጥሽ ኳስ መጫወት ላይ ብቻም ትኩረቷን አላደረገችም። ጎን ለጎን ትምህርቷን በሚገባ ትከታተል ነበር፡፡ ቡድኑ ራሱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠናከረ ሲመጣ ውድድር ያስፈልገው የነበረ ቢሆንም አዲስ አበባ ውስጥ ሌላ ክለብ ባለመኖሩ ወደ ድሬዳዋ ትምህርት ሲዘጋ በምድር ባቡር ወጪ ወደ ተጉዘው ከወንዶች ጋር የቅስቀሳ ውድድር እየተጫወቱ የሴቶች እግር ኳስ ከፍ ይል ዘንድ አስተዋጿቸውን በዚህ መልኩ በማበርከት ቀጥለዋል፡፡

የምድር ባቡር የሴቶች ክለብ ወደ ምስራቃዊቷ የሀገሪቷ ክፍል እያቀኑ መጫወት በመጀመራቸው ሁለተኛው የሴቶች ክለብ እንዲመሠረት አደረገ። ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ማክዳ የሚባል በአየር ኃይል ተቋም ይረዳ የነበረ ክለብ እንዲቋቋም መሠረቱን ጣለ። “የእኛ ቡድን ወደ ድሬዳዋ ሄዶ በሰራው ስራ ማክዳ የሚባል የሴቶች ቡድን ተቋቋመ። ከዛ ወደ አዲስ አበባ ስንመለስ አቶ ስለሺ ቤተመንግስት ጋር የነበረ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩ አሁን ሞተዋል፣ እነ አቶ ምስክር ያሉበት እቱ መላ ምቺ የሚባል ሦስተኛ ቡድን ደግሞ መጣ። ቡድኖች እየበዙ ሲመጡ እኛም ሞራላችን ከፍ እያለ መጣ። ውጤታማም ሆንን ክለብ ከመመስረት አልፈን ደግሞ ኮሚቴ መሠረትን።” በማለት የሴት ቡድኖችን ለማስፋፋት ስላደረጉት ሒደት ትገልፃለች፡፡

የሴቶች እግር ኳስ በደንብ እየዳበረ እና እያደገ እንዲመጣ ከተጫዋችነቷ ጎን ለጎን ኮሚቴ እንዲቋቋም ያደረገችው በለጥሽ ራሷ እና ጥቂት ተጫዋቾች እንዲሁም ሴቷችን ለማበረታታት ድጋፍ የሚያደርጉ ግለሰቦችን ያቀፈ ኮሚቴ ተቋቋመ። በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የቀድሞው የኦሜድላ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ገዛኸኝ ማንያዘዋል እና የበለጥሽ ወንድሞች አስፋው እና ተፈራ እንዲሁም ደግሞ ሀዋሳ ከተማን በወንዶች እግርኳስ ፕሪምየር ሊግ ሁለት ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ያደረጉት አሰልጣኝ ከማል አህመድ (በወቅቱ በመርካቶ ምስራቃዊት ሄዋን የሴቶች ቡድን መስራች እና አሰልጣኝ) የመሳሰሉ ግለሰቦች ነበሩ። እንዲህ እያለ መሠረቱን የጣለው የሴቶች እግርኳስ በግል ከመጫወት ተነስቶ ብዙሀኑን ሰብስቦ ወደ ክለብነት እየለወጠ መጣ። በምድር ባቡር የተጀመረው ጉዞ እቱ መላ ምቺ፣ ምስራቃዊት ሄዋን እያለ ወደ አስራ ስምንት የሚጠጉ የሴት ቡድን በመዲናይቱ እየተበራከቱ መጡ። ለዚህም ዕድገት ደግሞ ኮሚቴው መቋቋሙ ፍጥነቱን ጨምሮለታል፡፡

ምንም እንኳን በዛን ዘመን በፌዴሬሽን ዕውቅናን ያገኙ ቡድኖች ባይኖሩም በኮሚቴ ውስጥ አባል የሆነችው እና ምድር ባቡርን በተጫዋችነት ስታገለግል የቆየችው የያኔዋ አጥቂ ለምን ውድድር አናደርግም የሚል ሀሳብ በማንሳት ዋንጫ ተገዝቶ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጀ። “መርካቶ አካባቢ ኳስ ሜዳ የሚባል ነበር። እዛ ሜዳ ላይ ለምን አናከናውንም ብለን ተነሳን ፤ ውድድርም አዘጋጀን።” በማለት በብዙ ውጣ ውረድ አልፋ ቡድን ከማቋቋም በዘለለ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ስለተደረገበት ወቅት ታነሳለች። በአካባቢዋ ባሉ አንዳንድ ማህበረሰብም ሆነ በአባቷ ጫናዎች ቢበረክትባትም ሁሉንም ተቋቁማ ለስኬት ከመብቃት ወደ ኋላ ያስቀራት ግን አንዳችም ነገር አልነበረም፡፡ ምንም የላብ መተኪያ ባልነበረበት ያኔ ምድር ባቡር ያፈራቸውን በርካታ የወንድ ስመ ጥር ተጫዋቾችን ፈለግ እየተከተለች የአባቷን ዱላ እየተቋቋመች ለቁም ነገር የበቃችው እንስቷ ከተለያዩ ቡድኖች ጋር በክለቧ ቆይታዋ በመጫወት አሳልፋለች፡፡ “ድሬዳዋ ከማክዳ ጋር ነበር የመጀመሪያ ጨዋታችን። ከዛ በመቀጠል ግን መርካቶ ኳስ ሜዳ ላይ በተለይ ቅዳሜ እና ዕሁድ ኮሚቴ ከተቋቋመ በኃላ ጨዋታዎችን እናደርጋለን። በጣም ብዙ ተመልካቾች ተገኝተው ይመለከቱን ነበር። በመጀመሪያ ጨዋታችንም እኛ እና እቱ መላ ምቺ ለዋንጫ ደረስን፤ ከዛ ፌዴሬሽኖቹ የሴቶች እግርኳስ ምን ያህል ተመልካች እንዳለው መጥተው ይዩ አልን። ያኔ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሳይሆን የሸዋ እግር ኳስ መምሪያ በአዲስ አበባ ነበር ሚባለው ፤ የመምሪያው ፀሀፊ አቶ ሽመልስ መርኔ የሚባሉ አሉ። እሳቸውን የክብር እንግዳ አድርገን ጋበዝን ፤ የእኛ ቡድን ምድር ባቡር አሸነፍን። እሳቸውም የሰውን ፍላጎት ሲያዩ እዛው ‘ከዚህ በኃላ የሴቶች እግርኳስ እኛ ነን የምናዘጋጀው’ አሉ። ቴሴራም ተሰጠን፤ በዓመቱም ውድድር አዘጋጁልን። ከዛ በኃላ በቀጣዩ ጊዜ በአዲስ አበባ ስታድየም እኛ እና እቱ መላ ምቺ ለዋንጫ ደርሰን እኛ አሸንፈን ዋንጫ በላን። እንዲህ እንዲህ ሲል ነው የሴቶች እግር ኳስ ዛሬ ላይ የደረሰው።” ስትል ከተጫዋችነት አንስታ ለእግርኳሱ ዕድገት በኮሚቴ መዋቅር ውስጥ አልፋ ስላሳለፈችበት ጊዜያት በምድር ባቡር ቆይታዋ ስላሳካቻቸው በዋንጫ የታጀቡ ዓመታት ወደ ኃላ መለስ ብላ አውግታናለች፡፡

ከ1964 በምድር ባቡር የጀመረው የተጫዋችነት ህይወቷ ስምንት ዓመታትን አስቆጥሮ 1971 ላይ ግን ኳስን ልታቆም መገደዷን ትገልፃለች። “1971 ላይ ‘የሴት ኳስ ምን ይሰራል ?’ የሚል ሀሳብ መጣ እኛም ልምምድ እየሰራን ውድድር ይጠሩናል ብለን ስናስብ በቴሌቪዥን አንድ ነገር ሰማን። ‘ለምንድነው የሴቶች እግርኳስ የቆመው ?’ ተብሎ ሲጠየቅ ‘አይ በመውለድ ላይ ችግር ያመጣል ከአሁን በኋለ ውድድር አይደረግም’ የሚል መከራከሪያ መጣ። እኛም ስፖርት ኮሚሽን ሄደን ስሞታችንን ብናቀርም በእኛ አቅም የሚቻል አልሆነም ፤ አቆምን። ብዙዎቹ ወደ እጅ ኳስ ሲገቡ እኔ ግን እጅ ኳስንም መስራት አልፈለኩም እግርኳስን ብቻ መጫወት ስለነበረ ፍላጎቴ።” ስትል እግር ኳስን ሳትጠግብ በመንግሥት አስገዳጅነት ለማቋም የተገደደችበትን አጋጣሚ አውስታናለች፡፡

በሜዳ ላይ ጠንካራ እና እልህኛ እንደነበረች የሚነገርላት በለጥሽ ገብረማርያም ከእግርኳስ ባሻገር ትምህርቷን በሚገባ ተምራ በማጠናቀቋ ወደ ሜታ አቦ ተጉዛ ሰርታለች። በተለይ ሜታ አቦ ስፖርት ክለብ ውስጥም በፀሀፊነት በመስራት በተጫዋችነት ባይሆንም ዳግም ወደምትወደው ስፖርት መመለስ ቻለች። በሜታ አቦ ቆይታዋ በሸዋ ክፍለ ሀገር ውድድር ላይ ቡድኑ ጠንካራ ይዘት እንዲኖረው በማድረጉም ድርሻዋ የሚዘነጋም አልነበረም። በሒደት ራሷን በአስተዳደር ዘርፍም እያሳደገች ስትመጣ ፊፋ ሁለት ሴቶች ወደ ፌድሬሽን ኮሚቴ መግባት አለባቸው በማለቱ እሷም ይህን ጥሪ ተቀብላ በኢንጂነር ፀሀዬ አመራር ውስጥ ተቀላቀለች። አሁንም እግርኳስ በልቧ በመታተሙ የተለያዩ ስልጠናዎችን ከመውሰዷ በፊት በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን የእግርኳስ ውድድሮችን እና በተለይ ደግሞ የአፍሪካ ሻምፒዮናዎችን ስትመለከት ቆየች። እነኚህን ነገሮች በተደጋጋሚ ማድረጓም ወደ አሰልጣኝነቱ ለመግባት ላደረባት ፍላጎት መነሻ ሆኗታል፡፡ እኚህን ውድድሮች በቴሌቪዥን መስኮት መከታተሏ ቁጭት የፈጠረባት በለጥሽ የክለብ ውድድሮች ባይኖሩም ብሔራዊ ቡድን የማቋቋም ሀሳብ አቀረበች።

“ለፌዴሬሽኑ ይህን ሀሳብ አቀረብንና ተቀባይነት አገኘ። ነገር ግን ለብሔራዊ ቡድን የሚሆን አሰልጣኝ የለም። እኔ ቀረብ ስለምል ተመረጥኩ። ለብሔራዊ ቡድኑ ግብአት እንዲሆን የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ይደረግ ተባለና ከውድድሩ ላይ ለብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በመምረጥ እነሱን ይዘን በሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ናይጄሪያ ላይ ተሳተፍን። የእኛ ልጆች ክለብ ባይኖራቸውም ጥሩ ተሳትፎን አድርገን ልምድም አግኝተንበት ደረጃችንንም አይተንበት ተወዳድረን ተመለስን።” ስትል እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2002 ናይጄሪያ ላይ ተዘጋጅቶ በነበረው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ላይ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ስላገለገለችበት ጊዜ በትዝታ ነግራናለች፡፡

በሒደት የተለያዩ የአሰልጣኞች ስልጠናን ሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ በመውሰድ የአሰልጣኝነት ዕውቀቷን እየገነባች የመጣችው በለጥሽ በተለይ ከነአብርሀም መብራቱ እንዲሁም ሀዋሳ ከነማን በ1980ዎቹ ካሰለጠኑት የቀድሞው አሰልጣኝ ተገኝወርቅ ጋር ሆና በአፍሪካ ዞናል ኢንስትራክተርነት ስልጠናን በ90ዎቹ ኬንያ ላይ ወስዳለች። ስልጠናውንም አልፋ ሴት ኢንስተትራክርም ለመሆን በቅታለች። ከወንድ አሰልጣኞች ጋር በብሔራዊ ቡድን ደረጃ አብራ በመስራት ያገለገለችው በለጥሽ በተለይ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ እጅግ ጠንካራ ተፎካካሪ በሆነበት ወቅት ከአሰልጣኝ መለሰ ሸመና እና አሸናፊ በቀለ ጋር በጥምረት ቡድኑን በማሰልጠን ከጋና ጋር ለደረጃ ተጫውቶ አራተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ በቡድኑ ውስጥ የማይዘነጋን አሻራ ጥላ አልፋለች፡፡ “በጣም ጥሩ ቡድን ነበር ፤ ለዋንጫም የሚፎካከርም ጭምር ነበር። ከጋና ጋር በፍፁም ቅጣት ምት ተሸንፈን አራተኛ ብንወጣም በጣም ጥሩ ነገር አሳይተናል። የፀባይ ዋንጫን ይዘን መጥተናል። ከዚህ በኃላ ወደ ሀገሬ ስመለስ ግን ሌላ ስራ ስላለኝ ከስራዬ ጋር መሄድ አልቻለም። ወይ ስራዬን አልያም ስልጠናውን መምረጥ ነበረብኝ። ከስፖርቱ ይልቅ አሁን ያለሁበት ስራዬ የተሻለ ስለነበር ከማሰልጠኑ ልወጣ ችያለሁ።” ስትል በነበረባት ተደራራቢ የስራ ጫና ከምትወደው አሰልጣኝነት እንዴት ለመራቅ እንደተገደደች በቁጭት ትገልፃለች፡፡

ከአሰልጣኝነቱ ብትወጣም እስከ 2010 ድረስ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሴቶች ኮሚቴ ፣ የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲሁም ከ2005 ጀምሮ ደግሞ ካፍ ‘ተጫውተው ያለፉ በተለያዩ የእግር ኳስ ሙያ ውስጥ ያሉ ሴቶች የእግርኳስ ዳኞች ኮሚሽነር ይሁኑ’ በማለቱ በኮሚሽነርነትም ወሳኝ ጨዋታዎች ላይ ሰርታለች፡፡

በአሁኑ ሰዓት በሞሐ ኩባንያ እየሰራች የምትገኘው በለጥሽ ‘እግርኳስ የህይወቴ አንድ አካል ሆኖ ዘልቋል’ በማለት ለእግር ኳሱ ያላትን ጥልቅ ፍቅር ተናግራ አትጨርሰውም። ምንም በሌለበት ወቅት እግር ኳስን ሴቶች መጫወት አለባቸው በማለት ፈር የቀደደችው እንስቷ ዛሬ ላይ እግርኳሳችን በፈለገው ደረጃ ላይ መሆን ባይችልም ሴቶች በክለብ ታቅፈው መስራታቸው እና ተጠቃሚ ሆነው ስታይ የሚሰማትን ስሜት እንዲህ አጫውታናለች። “በጣም የሚገርመው ነገር ሴቶች በፕሪምየር መሳተፍ አለባቸው በማለት አዋሽ ላይ አንድ ስብሰባ ነበር። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ በአቶ ሳህሉ እና አቶ ተካ አስፋው ጊዜ በጣም ክርክር ነበር። አቶ ሳህሉ እና አቶ ተካ ግን እንደሴት ሆነው ካፍ ሊከሷችሁ ይችላሉ። ‘ይሄ ብር እኮ የወንድም የሴትም ነው። መንግስት በሚኒስቴርነት ሴቶችን እየሾመ እኛ በስፖርቱ ልናገላችሁ አንችልም ፤ ውድድሩ መደረግ አለበት። የመጨረሻ ውሳኔ ሴቶችን የማታሳትፉ ከሆነ የወንዶች ውድድር ውስጥ አትሳተፉም።’ ብለው መሪዎቹ ተናግረው ውሳኔ ሲወስኑ በማየቴ ብሞት እንኳን አይቆጨኝም፤ ስለ እውነት። ለምን መሰለህ እንዲህ ብዬ የምናገረው፤ አቋም ይዤ የነዚህን ሰዎች ውሳኔ ሰምቼ ክለብ ተመስርቶ ክለብ ሰፍቶ ሴቶቹ ደመወዝተኛ ሲሆኑ ሳይ ደስ አለኝ። በእኛ ጊዜ የነበረው ልጆቹ ተማሪዎች ናቸው። ያንን ሁሉ ችግር ልጆች ተቋቁመው የሚገርመው ያለቅሱ ነበር። ከተሸነፉ እራት አይበሉም ምሳ አይበሉ ያኔ የነበሩ ልጆች ሲሸነፉ በብሔራዊ ቡድንም የነበራቸው ሀገራዊ ስሜት ኃይለኛ ነው። አሁን ደግሞ አድጎ በክለብ ደረጃ የውስጥ ውድድር በተለያየ መልኩ መኖሩ በጣም ደስ ብሎኛል። ነገ ደግሞ ከዚህ የተሻለ ብሔራዊ ቡድን እናያለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።” ስትል ስለፈጠረባት የእግርኳሱ የድሮ እና የአሁኑ ስሜትን በደስታ ድምፅ ነግራናለች፡፡

ከእግር ኳሱ ብትርቅም አሁንም ዕድገቱ የሚያሳስባት በለጥሽ በሞሐ ድርጅት ከምርት ክፍል እስከ ቴክኒክ ክፍል ኃላፊነት ድረስ ሰርታለች አሁንም እየሰራች ትገኛለች። ባለትዳር ስትሆን ካሳደገቻቸው ከእህት ወንድሞቿ ልጆች ጋር ጤናማ በሆነ መልኩ ህይወቷን እየመራች እንደሆነ በመናገር የነበረንን ቆይታ አጠናቀናል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ