ወላይታ ድቻ ሦስት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ተስማማ

ቀደም ብለው አራት ወጣት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ተስማምተው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ሁለት የቀድሞ ተጫዋቾቻቸውን እና ግብ ጠባቂ ለማስፈረም በዛሬው ዕለት ከስምምነት ደርሰዋል፡፡

ዛሬ ለመፈረም ከተስማሙት መሐል ቀዳሚው አጥቂው ስንታየው መንግስቱ ነው፡፡ ከወላይታ ድቻ ታዳጊ ቡድን ተገኝቶ በዋናው ቡድን እስከ 2009 ድረስ ተጫውቶ ያሳለፈው ተጫዋቹ ወላይታ ድቻን ከለቀቀ በኃላ ለሀላባ ከተማ እና 2011 ደግሞ ለአርባምንጭ ከተማ በመጫወት አሳልፏል፡፡ የ2012 ቆይታውን በባህር ዳር ከተማ ካደረገ በኃላም በድጋሚ ወደ ልጅነት ክለቡ ተመልሷል፡፡

ሌላኛው ከሳምንት በፊት ተስማምቶ በዛሬው ዕለት የፈረመው የቀኝ ተከላካዩ አናጋው ባደግ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ለወላይታ ድቻ የተጫወተ ሲሆን ከዛም በመቀጠል ለድሬዳዋ ከተማ እና ደቡብ ፖሊስም አገልግሏል፡፡ ዘንድሮ ለመከላከያ ከተጫወተ በኃላ ዳግም የጦና ንቦቹን ከሦስት ዓመታት በኃላ መቀላቀል ችሏል፡፡

ሦስተኛው አዲስ ተጫዋች ሰዒድ ሀብታሙ ነው፡፡ ዘንድሮ በሊጉ ከታዩ ምርጥ ግብ ጠባቂዎች መሐል አንዱ መሆኑን በጅማ አባ ጅፋር ያሳየው የቀድሞው የአርባምንጭ ተጫዋቾች ከሳምንት በፊት መስማማት ወደቻለበት ድቻ የሁለት ዓመት ቅድመ ኮንትራት በመፈረም ዛሬ ተስማምቷል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

error: