የዝውውር መስኮቱ ከአስራ ስድስት ቀናት በኃላ ይከፈታል

የዝውውር መስኮቱ ቀደም ተብሎ ከመስከረም 2 ጀምሮ እንደሚከፈት ቢጠበቅም በአስራ ሦስት ተጨማሪ ቀናት ተራዝሞ በይፋ ከመስከረም 15 እስከ ታህሳስ 15 ድረስ ለሦስት ወራት ክፍት ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስቀድሞ የ2013 የውድድር ዘመን የዝውውር መስኮት ከመስከረም 2 እስከ ህዳር 25 ድረስ ይከናወናል ብሎ አስቀድሞ መግለፁ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ቀደም በዘገባችን ዝውውሩ እንደሚራዘም የጠቆምን ሲሆን አሁን ደግሞ መራዘሙ እርግጥ ሆኗል፡። መንግሥት ውድድሮች በይፋ የሚጀመሩበት ቁርጥ ያለ ቀን በጊዜ ባለመግለፁ እንዲሁም ፊፋም ትክክለኛውን የዝውውር ቀን ካልተገለፀበት ቅጣት በሀገራችን ሊያስተላልፍ ስለሚችል ማራዘም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የዝውውሩ መስኮቱ ከመስከረም 15 እስከ ታህሳስ 15 ባሉት ሶስት ወራት እንዲከናወን የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ መወሰኑን የፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

የዝውውር ቀኑ እንዲገለፅላቸው ተደጋጋሚ ጥያቄን ለፌዴሬሽኑ ሲያቀርቡ ለነበሩ ክለቦችም እፎይታን የፈጠረ በፊፋም የተመዘገበ ትክክለኛ ቀን መሆኑን ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!