የፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር አንደኛ መደበኛ ጉባዔ የዛሬ ውሎ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ዛሬ በኢንተርኮንትኔንታል አዲስ ሆቴል ከክለብ ተወካዮች ጋር ጉባዔውን አካሂዷል።

ጉባዔው ዋንኛ ትኩረቱን በ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ ማድረጉ የታወቀ ሲሆን ሀያ ሶስት ገፆች ባሉት የውድድር ደንብ ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ተደርጓል። የአክሲዮን ማኅበሩ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ፣ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኤልያስ ሽኩር እና የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጂራ ንግግር ያደረጉ ሲሆን

የቦርድ ሰብሳቢው መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በበኩላቸው በ2012 የተሰሩ እና የተከወኑ ተግባራት ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ በአፍሪካ ውድድር ተሳታፊ ስላለመኖሩ እና ሌሎች ከዚህ ቀደም የተወሰኑ ውሳኔዎች ላይ ማብራርያ ሰጥተዋል። ሊጉ እስኪቋረጥ ድረስ የነበረው የፀጥታ ሁኔታን በስኬትነት ሲያነሱ ከተሠሩ ተግባራት መካከል ሊጉ ኦፊሴላዊ መለያ (ሎጎ) እንዲኖረው ጨረታ ወጥቶ ሰማንያ ሺህ ብር ወጪ በማድረግ እንደተዘጋጀ፣ ለ2013 የውድድር ዘመን ከስፔን ላሊጋ ጋር በጥምረት ለመሥራት እና የኢትዮጵያን ፕሪምየር ሊግ ከሀገር ውጪ ለማስተዋወቅ፣ በቴሌቪዥንም ሆነ በሬዲዮ የቀጥታ ስርጭት እንዲኖረው ስለወጡ ጨረታዎች፣ ሥያሜ መብቱን ስለመሸጥ እና የመሳሰሉ ጉዳዮች አንስተው ማብራርያ ሰጥተዋል። የታሰቡት ሰየሥራዎች በታቀደላቸው ፍጥነት እንዳይጓዙ የነበሩ እክሎች ላይም ገለፃ አድርገዋል። ከክለቦች ጋር የሚደረግ ግንኙነት ኋላ ቀር መሆን፣ የክለቦች የተሟላ አደረጃጀት እና ከመንግሥት ተቋማት የተለየ የራሳቸው ሲስተም አለመኖር እና የመሳሰሉትን አንስተዋል።

የቦርድ ሰብሳቢው የ2012 የሥራ ክንውን ተግባራትን በዝርዝር ካብራሩ በኃላ የኮቪድ 19 ወረርሺኝን ለመከላከል የቀረበው የቅድመ ጥንቃቄ መመሪያ ሰነድ ዙሪያ የውድድር እና ስነ ስርዓት ሰብሳቢው ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉስ ገለፃ አድርገዋል፡፡ በነኚህ የቀረቡ ሰነዶች ላይ የክለብ ተወካዮች የራሳቸውን ምልከታ በማስቀመጥ ጥያቄን እያቀረቡ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ከጠዋቱ የውይይት መድረክ ቀጥሎ ከሰዓት ላይ 23 ገፆች ባሉት የተሻሻለው የክለቦች ደንብ ላይ ከውድድር እና ስነ ስርአት ኮሚቴው አባል አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል ማብራርያ ከቀረበ በኃላ ሰፊ የውይይት የጥያቄ እና መልስ መርሀ ግብሮች የተደረጉ ሲሆን በመጨረሻም በተዘጋጁ ሜዳዎች፣ የመለማመጃ ቦታዎች፣ ስለ ህክምና አሰጣጥ እና አተገባበር በውይይቱ ከተነሳ በኃላ ምሽት 12፡30 ድረስ ቆይታን አድርጎ የውድድር ደምቡ በአብላጫ ድምፅ ፀድቆ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

ይህ ጉባዔ ነገም ሲቀጥል ኩባንያውን ለቀጣዩ ሦስት ዓመታት የሚመሩ አካላትን መምረጥ፣ የውድድር ቀን እና ሥፍራዎችን መወሰን ላይ እንደሚያተኩር ሰምተናል። ከሰዓት ላይ ደግሞ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ይኖራል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!