በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና በመጨረሻ ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ከፋሲል ከነማ ጋር 1ለ1 ተለያይቷል።
ከሽንፈት የተመለሱት ዐፄዎች ባለፈው ከተጠቀሙበት አሰላለፍ ባደረጉት የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል፣ ኪሩቤል ዳኜ፣ ሐብታሙ ተከስተ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል አስወጥተው ግብ ጠባቂ ዮሐንስ ደርሶ፣ ዮናታን ፍስሀ፣ አሚር ሙደሲር እና ማርቲን ኬዛን ሲያስገቡ በአንፃሩ ነብሮቹ ድል አድርጎ ከተመለሰው ስብስባቸው የሦስት ተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ግብ ጠባቂ ያሬድ በቀለ፣ ፀጋአብ ግዛው እና ተመስገን ብርሀኑ አሳርፈው ግብጠባቂ ስንታየሁ ታምራት ፣ ሰመረ ሀፍታይ እና ኢዮብ አለማየሁን አስገብተዋል።
በዋና ዳኛ ማኑሄ ወልደፃድቅ ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ ፋሲል ከነማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ጥሩ አጀማመር ሲያደርጉ 5ኛው ደቂቃ ላይም ማርቲን ኬዛ በግራ መስመር አክርሮ በመታው እና ግብጠባቂው ስንታየሁ ባመከነበት የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገዋል። በ17ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ቀዳሚ የሆኑበትን ጎል ከቅጣት ምት አግኝተዋል። የቅጣት ምት ቀበኛው ጌታነህ ከበደ ራሱ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ በእርጋታ የግብጠባቂውን አቋቋም አይቶ ኳሷን መረቡ ላይ አሳርፎታል።
በ30ኛው ደቂቃ ሌላ ሁለተኛ ጎል ለማስቆጠር ተቃርበው የነበሩት ፋሲሎች በጥሩ የማጥቃት ሽግግር በረከት ወደ ውስጥ የላከውን ጌታነህ አመቻችቶ ያቀበለውን ማርቲን ኬዛ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂ ስንታየሁ በውስጥ እግር ወደ ውጭ አውጥቶበታል።
የአጋማሹ የመጨረሻ አምስት ደቂቃዎች ከነበሩበት የተቀዛቀዘ ሂደት ወደ እንቅስቃሴው የገቡት ነብሮቹ የጎል ዕድሎችን መፍጠር ጀምረዋል። በ41ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብሎች ወደ ማጥቃቱ ሽግግር በመግባት ብሩክ በየነ ተከላካይ ቀንሶ ነፃ ኳስ የሰጠውን ኢዮብ አለማየሁ ሳይጠቀምበት የቀረው የምታስቆጭ አጋጣሚ ካመለጣቸው ከአራት ደቂቃ በኋላ ሰመረ ሀፍታይ ከቀኝ መስመር ወደ ግራ በመግባት በግራ እግሩ የመታውን ግብ ጠባቂው ዮሐንስ ደርሶ አምክኖበታል።
ከዕረፍት መልስ ብሩክ በየነ እና ሰመረ ሀፍታይን አስወጥተው ተመስገን ብርሀኑ እና ደስታ ዋሚሾ በማስገባት ጨዋታውን የጀመሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ተሻሽለው በመቅረብ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን በማደራጀት አደጋ ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በዚህ ሂደት በ56ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ተመስገን ብርሃኑ ሳይጠቀምበት የቀረው ዕድል ነብሮቹን ወደ ጨዋታ ለመመለስ የምታስችል ጥሩ አጋጣሚ ነበረች።
በሀድያዎች የበላይነት በቀጠለው ጨዋታ ዐፄዎቹ በመጀመርያው አጋማሽ ከነበራቸው የበላይነት ዝቅ ክፍተት ለመቅረፍ የተጫዋች ቅያሪ ቢያደርጉም ብዙም የተለየ ነገር መፍጠር አልቻሉም ነበር። በአንናፃሩ ነብሮቹ 76ኛው ደቂቃ ፋሲሎች በራሳቸው የሜዳ ክፍ በቅብብሎሽ የፈጠሩትን ስህተት ተከትሎ ተመስገን ብርሀኑ አግኝቶ በጥሩ መንገድ ተከላካዮች በማለፍ የፈጠረውን ዕድል የመጨረሻ ኳስ አጠቃቀም ትክክል ያልነበረ በመሆኑ ግብጠባቂው ዮሐንስ ደርሶ በቀላሉ ይዞበታል።
ጫና በመፍጠር በተደጋጋሚ በፋሲል ከነማ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ሀድያዎች በስተመጨረሻም የጥረታቸው ፍሬ የሆነ የአቻነት ጎል 88ኛው ደቂቃ አስቆጠረዋል። ከቀኝ መስመር ተቀይሮ የገባው ማሞ አየለ ወደ ውስጥ በመግባት ለተመስገን የሰጠውን ተመስገን ለኢዮብ አቀብሎት በጥሩ አጨራረስ ወደ ጎልነት ቀይሮታል። በጨዋታው ተጨማሪ ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ከቅጣት ምት የፈጠረውን አደጋ አስመልክቶን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 1-1 አቻ ውጤት ተገባዷል።