በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ የሆነውን የውድድር ዓመቱ እጅግ ተጠባቂ ጨዋታ ነገ ይከናወናል።
በሰንጠረዡ አናት ተከታትለው የተቀመጡ ቡድኖችን የሚያገናኛው ጨዋታ ውጤት ለሁለቱም ከዋንጫ ጋር የተቆራኘ ተመሳሳይ ትርጉም ይኖረዋል። ለመሪው ኢትዮጵያ መድን አሁን ያለውን የዘጠኝ ነጥብ ልዩነት ይበልጥ አስፍቶ በጊዜ ዋንጫውን በእጁ ለማስገባት የሚያደርገው ጥረት ውስጥ የሚከወን ጨዋታ ሲሆን ለኢትዮጵያ ቡና ደግሞ የነጥብ ልዩነቱን ወደ ስድስት አጥብቦ ለዋንጫ በሚደርገው ፍልሚያ ውስጥ ተስፋን የሚያልምበት ጨዋታ ይሆናል።
በሀምሳ አንድ ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቡናማዎቹ ባለፉት አራት ጨዋታዎች በመደዳ ድል ማድረጋቸው ከውድድር ዓመቱ ወሳኝ ጨዋታ በፊት በሥነ ልቦናው ጠንክረው እንዲቀርቡ የሚያደርጋቸው ጉዳይ ነው። በሊጉ በፈጣን ‘Counter pressing’ ከሚታወቁ ቡድኖች በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ቡናማዎቹ ከኳስ ውጭ ጠጣር ውቅር ገንብተዋል፤ ይህንን ተከትሎም ከነገው ተጋጣሚያቸው ቀጥሎ ጥቂት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀታቸው የቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎን ነው። ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ከተካሄዱ አስራ አንድ ጨዋታዎች ውስጥ በዘጠኙ መረቡን በማስከበር ከሊጉ ቀዳሚ ሲሆን በነገው ዕለትም ከውድድር ዓመቱ አጋማሽ በኋላ በተከናወኑ አስራ አንድ ጨዋታዎች አስራ ሰባት ግቦች ካስቆጠረው የተጋጣሚው የፊት መስመር የሚያደርጉት ፍልምያ ጨዋታው አጓጊ ያደርገዋል።
የአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ቡድን በመከላከሉ ረገድ ያለውን ጥንካሬ ውጤቱን አስጠብቆ እንዲወጣ ብያደርገውም በጨዋታዎች ከአንድ ግብ በላይ ያለ ማስቆጠር ችግሩ አሁንም ጨርሶ አልቀረፈም።
በውድድር ዓመቱ የ30 ሳምንታት ቆይታ በስድስት መርሐ-ግብሮች ብቻ ከአንድ ግብ በላይ ያስቆጠረው ቡድኑ በነገው ዕለት የሊጉ ጠንካራና ጥቂት ግቦች ያስተናገደውን ክለብ እንደመግጠሙ በአፈፃፀም ረገድ ያለበት ድክመት መቅረፍ ይኖርበታል። በነገው ጨምሮ በቀጣይ መርሐ-ግብሮችም ላሉበት የፉክክር ደረጃ የሚመጥን የማጥቃት ጥንካሬ መላበስ ከቡናማዎቹ የሚጠበቅ ነው።
በዘጠኝ ነጥብ ልዩነት ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች በመሪነቱ ተደላድለው ዋንጫውን በእጃቸው ለማስገባት በነገው ጨዋታ ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው ።
ዋንጫውን በጊዜ ለማግኘት በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ነገ የዋንጫውን አንድ እጀታ ለመጨበጥ የሚያስችላቸውን ወሳኝ ጨዋታ የሚያደርጉት መድኖች በማጥቃቱም ይሁን በመከላከሉ ረገድ ያላቸውን ጥንካሬ ዘለግ ላሉ የጨዋታ ሳምንታት መሪነቱን እንዲቆናጠጡ አስችሏቸዋል፤ በሊጉ በርከት ያሉ ግቦች በማስቆጠር (38) እንዲሁም ጥቂት ግቦች በማስተናገድ (12) ቀዳሚ የሆነው ቡድኑ የውድድር ዓመቱ ጉዞውን በዋንጫ ለማጀብ በነገው የዓመቱ እጅግ ወሳኝ የሆነው ጨዋታ ከወትሮው ለየት ባለ ጥንካሬ መቅረብ ግድ ይለዋል። ከሌሎች የሊጉ ክለቦች የተሻለ ወጥ የሆነ ብቃት ማሳየት የቻሉት መድኖች በአዳማ እና ሀዋሳ ቆይታቸው በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ የጣሉበት አጋጣሚ የለም፤ በተለይም በአስራ አንድ ጨዋታዎች አስራ ሰባት ግቦች ያስቆጠሩበት ሁለተኛው ዙር በብዙ ረገድ የተሻሻሉበት ነበር። በነገው ዕለትም በመጨረሻዎች አራት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደው እና በሁለተኛው ዙር በርከት ባሉ ጨዋታዎች መረቡን ባለማስደፈር ቀዳሚ ከሆነው የኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ መስመር የሚያደርጉት ፍልምያ የጨዋታውን ውጤት የመወሰን አቅም አለው።
በጥቅሉ ተጠባቂው ጨዋታ በዋንጫ ፉክክሩ ዋነኛ ተፋላሚዎችን ማገናኘቱ እንዲሁም ሁለቱም ቡድኖች በሁለተኛውን ዙር ተመሳሳይ ነጥብ በማስመዝገብ በተቀራራቢ ወቅታዊ ብቃት መገኘታቸው መርሐ-ግብሩ አጓጊ ያደርገዋል።መድኖች ድል አድርገው የዋንጫውን አንድ እጀታ ይጨብጣሉ ? ወይስ ኢትዮጵያ ቡናዎች የነጥብ ልዩነቱን ወደ ስድስት ዝቅ አድርገው የዋንጫ ተስፋቸውን ያለመልማሉ ? የሚሉትን ጥያቄዎች መልስም ነገ የምናየው ይሆናል።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ ከአንድ ጨዋታ ቅጣት ሲመለስ ተከላካዩ ወልደአማኑኤል ጌቱም ከጉዳት መልስ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል። የትከሻ ህመም ላይ የሚገኘው አጥቂው አንተነህ ተፈራ ፣ ጠንከር ካለው ጉዳት ያላገገሙት እያሱ ፈጠነ እና መላኩ አየለ በጉዳት አሁንም አይኖሩም። በኢትዮጵያ መድን በኩል ደግሞ መሐመድ አበራ በጉዳት መሰለፉ አጠራጣሪ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 30 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 13 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መድን 8 ጊዜ አሸንፏል ፤ 9 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና 48 ጎሎች ሲያስቆጥር ኢትዮጵያ መድን 33 ጎሎች አስቆጥሯል።