ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡናዎች የዋንጫ ፍልሚያውን አጓጊ ማድረግ የቻሉበትን ድል አስመዝግበዋል

ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡናዎች የዋንጫ ፍልሚያውን አጓጊ ማድረግ የቻሉበትን ድል አስመዝግበዋል

ቡማዎቹ በራምኬል ጀምስ ብቸኛ ግብ የሊጉን መሪ ኢትዮጵያ መድንን በማሸነፍ በመካከላቸው ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ስድስት ማጥበብ ችለዋል።


የሐዋሳ ቆይታውን አጠናቆ ወደ ተረኛ አዘጋጅ ከተማ ያቀናው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በ31ኛ ሳምንት መርሐግብር በአዳማ ከተማ ጅማሬውን አድርጓል። ምሽት 12:00 ሲል ተጠባቂውን እና በሊጉ አንደኛ እና ሁለተኛ ሁነው ለዋንጫ ክብር የሚፋለሙትን ኢትዮጵያ ቡናና  ኢትዮጵያ መድንን አገናኝቷል። ኢትዮጵያ ቡናዎች በሐዋሳ የመጨረሻ ጨዋታቸው ላይ አዳማ ከተማን 2-0 ካሸነፉበት አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ቅያሪ ያደረጉ ሲሆን ሚኪያስ ፀጋዬን በስንታየሁ ወለጨ ሲቀይሩ በተቃራኒው ኢትዮጵያ መድኖች መቐለ 70 እንደርታን በአቡበከር ሳኒ ብቸኛ ግብ 1-0 ካሸነፉበት አሰላለፍ ዳዊት አውላቸውን በአዲስ ተስፋዬ በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በአሳቴዩ ስታዲየም ተጠባቂው ጨዋታ በደጋፊዎች ሕብረ ዜማ ታጅቦ ጅማሬውን አድርጓል። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የሆነ እንቅስቃሴ እና የኳስ ፍሰትን ያስመለከተን ሲሆን በኳስ ቁጥጥሩ እና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ ረገድ ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻሉ ነበሩ።

በመጀመሪያው 15 ደቂቃዎች ላይ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ያለቀላቸውን ሶስት የግብ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። 12ኛው ደቂቃ ላይ ከተከላካዮች በረጅሙ የተሻገረውን እና ስንታየሁ ወለጬ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ አማኑኤል አድማሱ ሳጥን ውስጥ የመታውን ኳስ አቡበከር ኑራ መልሶበታል። በተመሳሳይ 14ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል አድማሱ ያቀበለውን ኳስ ለግቡ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው ኮንኮኒ ሀፍዝ የመታው ኳሱ በአቡበከር ኑራ አስደናቂ ችሎታ ምክንያት ጎል ከመሆን ድኗል። ከአንድ ደቂቃ በኋላ በደጋሚ መልሰው ያገኙትን ኳስ ዲቫይን ዋቹኩዋ ከርቀት በመሆን ወደ የግቡን ጠርዝ አስደግፎ የመታውን ኳስ ግብጠባቂው አቡበከር ኑራ እንደ አሞራ ተወርውሮ ኳሷን መቆጣጠር ችሏል። እነዚህም ሙከራዎች ለቡናማዎቹ እጅግ አስቆጪ ነበሩ።

በጨዋታው ጅማሬ ላይ መረጋጋት ይጎላቸው የነበሩት ኢትዮጵያ መድኖች ከ15 ደቂቃዎች በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ በመመለስ በፈጣን ሽግግር ወደ ግብ መድረስ የቻሉትን የቡና ተጫዋቾች ለተወሰኑ ደቂቃዎች መቆጣጠር ቢችሉም 43ኛው ደቂቃ ላይ የመድኖችን የመከላከል አጥር በመናድ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ በመድን ተጫዋች ተጨርፎ ያገኘውን ኳስ ራምኬል ጀምስ በእግሩ መቶ በማስቆጠር በተከታታይ ጨዋታዎች ተከታታይ ሁለተኛ ግቡን ማስቆጠር ችሏል። ይህንንም ተከትሎ የመጀመሪያው አጋማሽ በቡናማዎቹ 1-0 መሪነት ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ኢትዮጵያ መድኖች መሻሻሎችን አድርገው ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን የነበረባቸውን ብልጫ በመቀነስ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ ጨዋታን አስመልክተውናል። ኢትዮጵያ ቡናዎች መከላከል ላይ ትኩረት በማድረግ በመልሶ ማጥቃት የሚገኙ ኳሶችን ፈጣን በሆነ ሽግግር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን ኢትዮጵያ መድኖች በበኩላቸው በመስመር አጥቂዎቻቸው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል።

ይሄ ነው የሚባል ዒላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ሳያስመለክተን ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ያስቆጠረው  አጋማሽ ጫናዎችን ፈጥረው የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ያለ የሌለ ሀይላቸውን አሟጠው የሚጠቀሙት መድኖች 83ኛው ደቂቃ ላይ እጅግ ለግብ የቀረበን ሙከራ በአለን ካይዋ እና ወገኔ ገዛህኝ አማካኝነት ሙከራ ማድረግ ቢችሉም በግብጠባቂው እና በተጫዋቾች ተጋድሎ ግብ ከመሆን ታድገውታል።

አንድ ግብ አስቆጥረው ያንን በማስጠበቅ በሚገርም የመከላከል ብቃት ለመድን አጥቂዎች ፈተና በመሆን ቡናማዎቹ ኢትዮጵያ መድንን 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በመካከላቸው ያለውን ነጥብ ማጥበብ ችለዋል።