ኤሌክትሪክ በሊጉ ለመቆየት የሚያደርገውን ጉዞ ለማሳካት መቻል ደግሞ ደረጃውን ለማሻሻል የሚያደርጉት ጨዋታ ቢሾፍቱ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ሜዳ ይከናወናል።
ሦስት ድሎች እንዲሁም ተከታታይ አምስት የአቻ ውጤቶች በድምሩ በስምንት የጨዋታ ሳምንታት ሽንፈት ሳይቀምሱ ከዘለቁ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈቶች ያስተናገዱት መቻሎች በተሻለ ደረጃ የውድድር ዓመቱን ለማገባደድ ድልን እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በአርባ አራት ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቻሎች በሊጉ በርከት ያሉ ግቦች በማስቆጠር ከሻምፒዮኑ መድን እና ባህር ዳር ከተማ ቀጥለው ከሀዋሳ ከተማ ጋር በጣምራ በ3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ቢችሉም በቅርብ ሳምንታት ግን የግብ ማስቆጠር አቅማቸው ተቀዛቅዟል። ምንም እንኳን የቡድኑ የፊት መስመር ብቃት ቀድሞውንም የወጥነት ችግር ቢኖርበትም ባለፉት መርሐግብሮች ግን ጉልህ የአፈፃፀም ችግር ተስተውሎበታል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦችን ያስቆጠረው ቡድኑ አሁንም ዕድሎች እየፈጠረ መቀጠሉ በበጎነቱ የሚነሳለት ቢሆንም ከስምንት መርሐግብሮች በኋላ ድል አድርጎ ደረጃውን ለማሻሻል እንቅስቃሴውን በግቦች ማጀብ ይኖርበታል።
በወራጅ ቀጠናው ላይ ካሉት መቐለ 70 እንደርታ እና አዳማ ከተማ ጋር ተመሳሳይ ሰላሣ ስምንት ነጥብ የሰበሰበው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቆ ከአስጊው ቀጠና ለመውጣት የሚያደርገውን ሩጫ ለማፋጠን ነገ እጅግ ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናል።
ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከወላይታ ድቻው ወሳኝ ድል በኋላ ቀጥተኛ ተፎካካሪዎቻቸው ከሆኑት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ፋሲል ከነማ ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ በአሁናዊ የደረጃ ሰንጠረዥ መሰረት በሊጉ የሚያቆያቸው ደረጃ ከያዙት ክለቦች አንፃር ሲታዩ ወደ ወራጅ ቀጠናው የመግባት አደጋ ተቃርበው ይታያሉ።
ኤሌክትሪኮች በመደዳ ከገጠሟቸው ሦስት ሽንፈቶች በኋላ በተከናወኑ አምስት መርሐግብሮች ውስጥ በአንድ አጋጣሚ ብቻ ሽንፈት በማስተናገድ ከተከታታይ ነጥብ መጣል ቢላቀቁም በጨዋታዎቹ ማግኘት ከሚገባቸው አስራ አምስት ነጥብ ውስጥ ማሳካት የቻሉት ስድስቱን ብቻ ነው። ቡድኑ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ወርቃማ ዕድል ባገኘባቸው ከቅርብ ተፎካካሪዎቹ ጋር ባደረጋቸው የመጨረሻዎቹ ሁለት መርሐ-ግብሮች ላይ ነጥብ መጣሉም ይበልጥ አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል። የቡድኑ የቅርብ ሳምንታት ድክመት በተመሳሳይ መንገድ የሚገለፅ ሲሆን የማጥቃት አጨዋወታቸው ችግርም ዋነኛው ደካማ ጎን ነው።
ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ላይ በሦስቱ ኳስና መረብ ሳያገናኝ ወጥቶ ሁለት ግቦች ብቻ ከማስቆጠሩም በተጨማሪ በጨዋታዎቹ የፈጠራቸው ዕድሎች ጥቂት መሆናቸውም የዚህ ማሳያ ነው። ይህንን ተከትሎ ለውጤት መጥፋቱ እንደ ዋነኛ ችግር የሚጠቀሰው የማጥቃት አጨዋወታቸው ማሻሻል የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ቀዳሚ የቤት ስራ ይሆናል።
በመቻል በኩል ተከላካዩ ፍሪምፖንግ ሜንሱ በጉዳት ምክንያት እንዲሁም በብሔራዊ ቡድን ግዳጅ ምክንያት ከቡድኑ ጋር የማይገኘው የግብ ዘቡ አሊዮንዚን ናፊያን በተመሳሳይ በጉዳት ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ባለመመለሱ ነገ ቡድናቸውን የማያገለግሉ ሲሆን አስቻለው ታመነም ቅጣቱን ባለመጨረሱ ከነገው ጨዋታ ውጪ እንደሆነ ታውቋል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል አሸናፊ ጥሩነህ ከቅጣት ሲመለስ ሄኖክ ገብረህይወት በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጭ ነው። የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ለነገው ወሳኝ ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 29 ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ 10 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መቻል 5 አሸንፎ በ14 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። መቻል 32 ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ ደግሞ 43 ግቦች አሉት።