በዘንድሮው አመት የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ መሆኑን ያረጋገጠው ሸገር ከተማ አምስት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።
በአሰልጣኝ ድሪባ ጃምቦ እየተመሩ ባሳለፍነው ዓመት የሴቶች ከፍተኛ ሊግ የሻምፒዮንነት ክብር ማሳካት የቻሉት ሸገር ከተማዎች ተፎካካሪነታቸውን በፕሪሚየር ሊጉ ለማስቀጠል በንቃት ዝውውሩ ላይ እየተሳተፉ ይገኛል። የአሰልጣኙን ውል በማደስ ወደ ስራ የገቡት ሸገሮች ተጨማሪ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረም ችለዋል።
በሀዋሳ እና በመቻል ጥሩ ጊዜያትን ማሳለፍ የቻለችው እንዲሁም በብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለችው፤ በጉዳት ምክንያት ረዘም ላለ ጊዜ ከሜዳ ብትርቅም በዘንድሮው የውድድር አመት በአርባምንጭ ከተማ ያሳለፈችው በሊጉ ረዘም ያለ ልምድ ባለቤት ሕይወት ረጉ ለአንድ አመት በሚቆይ ውል ለሸገር ከተማ ፊርማዋን በይፋ አኑራለች።
በሀዋሳ ከተማ እና በኢትዮ ኤሌክትሪክ የምናውቃት የዘንድሮውን የውድድር አመት በድሬዳዋ ያሳለፈችው የተከላካይ አማካዩዋ እታለም አመኑ ሌላኛዋ ቡድኑን የተቀላቀለች ተጫዋች መሆን ችላለች።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አዲስ አበባ ከተማ ፣ አርባምንጭ ከተማ፤ እንዲሁም ያለፉትን ሁለት ዓመታት በመቻል ያሳለፈችው የፊት መስመር ተጫዋቿ ቤተልሔም ታምሩ ለአንድ ዓመት በሚቆይ ውል ሸገር ከተማን ተቀላቅላለች::
በሙገር ስሚንቶ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ በንግድ ባንክ፣ በአዳማ ከተማ እና በአዲስ አበባ ከተማ መጫወት የቻለችው ያሳለፍነውን የውድድር አመት በአርባምንጭ ከተማ ያሳለፈችው ተከላካዩዋ ሰብለ ቶጋ ሌላኛዋ ፈራሚ ሆናለች።
በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ጥሩ ጊዜያትን ያሳለፈችው እንዲሁም ላለፉት ሁለት ዓመታት ከሊጉ ሻምፒዮን ንግድ ባንክ ጋር የዋንጫን ክብር ማሳካት የቻለችው አማካዩዋ ሶፋኒት ተፈራ ለአንድ ዓመት በሚቆይ ውል አዲስ አዳጊውን ክለብ ተቀላቅላለች።