ዐፄዎቹ ዋና አሰልጣኝ ለማግኘት ከጫፍ ደርሰዋል

ዐፄዎቹ ዋና አሰልጣኝ ለማግኘት ከጫፍ ደርሰዋል

ከአሰልጣኝ ውበቱ ጋር በስምምነት የተለያዩት ፋሲል ከነማዎች አዲስ አሰልጣኝ ለማግኘት ተቃርበዋል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከስሑል ሽረ ጋር ያሳለፈውን ካሜሮናዊ ግብ ጠባቂ ሞየስ ፖዎቲ ለማስፈረም ከስምምነት የደረሱት ዐፄዎቹ የቡድኑን ዋና አሰልጣኝ ለመቅጠር ከሰሞኑን ስማቸው ከተለያዩ አሰልጣኞች ጋር ሲነሳ ሰንብቷል።

ሶከር ኢትዮጵያ አሁን እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በቀር በክረምቱ የዝውውር መስኮት ስማቸው ከተለያዩ ክለቦች ጋር ሲያያዝ የቆዩት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ፋሲል ከነማን ለማሰልጠን ከጫፍ ደርሰዋል። ባለፉት ቀናት ከክለቡ የበላይ አመራር ጋር ውይይት ሲያደርጉ የቆዩት አሰልጣኙ ድርድሩ በአመዛኙ በስምምነት በመጠናቀቁ ዐፄዎቹን ለመረከብ ከጫፍ ሲደርሱ በቀሩ አንድ አንድ ነገሮች ለመወያየት ነገ ቀጠሮ መያዛቸውን ሰምተናል።

ዘለግ ላሉ ዓመታት በአሜሪካ ኑሯቸው ካደረጉ በኋላ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ደደቢት፣ ድሬዳዋ ከተማ ፣ መቐለ 70 እንደርታ ፣ ወልዋሎ ዓዲግራት፣ መቻል እና ሀዲያ ሆሳዕናን ያሰለጠኑት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በቅርብ ቀናት በይፋ ቡድኑን ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል።