ጀግኒት ካፕ በነገው ዕለት ጅማሮውን ያደርጋል

ጀግኒት ካፕ በነገው ዕለት ጅማሮውን ያደርጋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች መካከል የሚደረገው የመጀመሪያው የጀግኒት ካፕ ውድድር ነገ ይጀምራል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከጀግኒት ፕሮሞሽን እና ኢቨንት እንዲሁም ከአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የሚያዘጋጁት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የሚሳተፉበት የቅድመ ውድድር ዝግጅት አካል የሆነ ውድድር ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም መደረግ ይጀምራል።

ከነሐሴ 12 እስከ ነሐሴ 22 ድረስ በስድስት የሊጉ ክለቦች መካከል የሚደረገው ውድድር በተለይ ኢትዮጵያን ወክሎ ለሚወዳደረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም ለሌሎች የሊጉ የሴቶች ክለቦች ጥሩ የውድድር መዘጋጃ ጊዜ እንዲሆናቸውና ተጫዋቾችም አቅማቸውን የሚያሳዩበት፣ ለብሔራዊ ቡድኑ የሚታዩበት ብሎም ተመልካቹን የሚያዝናኑበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

ተሳታፉ ቡድኖቹ በሁለት ምድቦች የተከፈሉ ሲሆን በምድብ አንድ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ መቻል እና ቦሌ ክፍለከተማ ሲደለደሉ በምድብ ሁለት ደግሞ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ልደታ ክፍለከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ተመድበዋል።

ውድድሩ ነገ ጅማሮውን ሲያደርግም 5 ሰዓት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመቻል 7 ሰዓት ደግሞ ልደታ ክፍለከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚገናኙ ይሆናል።