ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሦስት ተጫዋቾችን ውል አራዝሟል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሦስት ተጫዋቾችን ውል አራዝሟል

በዝውውር መስኮቱ ድምጹን አጥፍቶ የነበረው ንግድ ባንክ የሦስት ነባር ተጫዋቾቹን ውል በማራዘም እንቅስቃሴ ጀምሯል።

ከዓመታት በኋላ ወደ ሊጉ ባደገበት 2016 የሊጉ ቻምፒየን መሆን የቻለው በአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ግን ፈታኝ ጊዜ ማሳለፉ ይታወሳል። ሆኖም ቡድኑ በክረምቱ የዝውውር መስኮት የሦስት ነባር ተጫዋቾቹን ውል በማራዘም ተሳትፎ ማድረግ ጀምሯል።

ውሉን ያራዘመው የመጀመሪያው ተጫዋች እንዳለ ዮሐንስ ሲሆን የቀድሞው የአዳማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ሀምበርቾ ተጫዋች በአሁኑ ቡድኑ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሦስተኛ ተከታታይ ዓመት ለመቆየት ተስማምቷል።

ሌላኛው ተጫዋች ደግሞ ከሀዋሳ ፕሮጀክት ተመልምሎ ከመጣ በኋላ በንግድ ባንክ ታዳጊ እና ተስፋ ቡድን እንዲሁም ባለፉት ሁለት ዓመታት በዋና ቡድን ተጫውቶ በብዙ ጨዋታዎች የማሸነፊያ ጎሎችን ያስቆጠረው ወጣቱ ዳዊት ዮሐንስ ነው።

ቡድኑ በተጨማሪም የዮናስ ለገሰን ውል ለተጨማሪ ዓመት አራዝሟል።