በሦስተኛው የጨዋታ ሳምንት መጀመሪያ ቀን ላይ የሚካሄዱ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ አርባ ምንጭ ከተማ
ነጥብ ተጋርተው የመጡትን ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ 7፡00 ሲል ይጀምራል። ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ኤሌክትሪኮች ከ ሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያለግብ የተለያዩ ሲሆን በተመሳሳይ አዞዎቹ ከባህር ዳር ከተማ ጋር 1-1 መለያየታቸው የሚታወስ ሲሆን በዛሬ ጨዋታ የ 3 ነጥብ ባለቤት ማን ይሆናል የሚለው ተጠባቂ ያደርገዋል።
በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ካደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ መሰብሰብ የቻሉ ሲሆን በአጥቂ ክፍል ያለባቸውን ድክመቶች በማሻሻል የዛሬውን ጨዋታ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተመሳሳይ በአሰልጣኝ በረከት ደሙ የሚመሩት አርባ ምንጭ ከተማዎች ካደርጓቸው ሁለት ጨዋታዎች በሁለቱም ነጥብ የተጋሩ ሲሆን የመጀመሪያ ሦስት ነጥባቸውን ለማሳካት በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ ያለባቸውን ደካማ ጎን አስተካክለው ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል አብዱላሂ አላዩ እና ቤዛ መድህን በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ ጉዳት ላይ የሰነበቱት አበል ሀብታሙ፣ ሚኪያስ ካሳሁን እና አብዱልመጅድ ሁሴን ወደ ልምምድ መመለሳቸው ሲታወቅ ለዛሬው ጨዋታ የመድረሳቸው ነገር አጠራጣሪ ነው። በአርባ ምንጭ ከተማ በኩል ጸጋየ አበራ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ሲታወቅ በኃይሉ ተስፋየ እና አንዱዓለም አስናቀ አሁንም በጉዳት ምክንያት የማይሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 18 ጊዜ ተገናኝተዋል። ኤሌክትሪክ 7 ሲያሸንፍ አርባምንጭ 6 አሸንፏል፤ ዘአምስት ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ኢትዮ ኤሌክትሪክም ሆነ አርባምንጭ ከተማ እኩል 22 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።
ምድረ ገነት ሽረ ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ
ወልዋሎዎች ካስተናገዱት ተከታታይ ሽንፈት በመውጣት ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እንዲሁም ምድረ ገነት ሽረዎች ከነጥብ መጋራት በኋላ እንደ መጀመሪያው ሳምንት ባለድል ለመሆን ከቀኑ 9:00 ሲል ይፋለማሉ።
በዚህ ዓመት ካደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ውስጥ በሁለቱም ሽንፈት ያስተናገዱት ቢጫ ለባሾቹ ወልዋሎዎች አምና ያሳዩትን ደካማ አቋም ዘንድሮም እየደገሙት ያሉ ይመስላል። በመጀመሪያው ሳምንት በ ሲዳማ ቡና ከደረሰባቸው ሽንፈት በኋላ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በ ፋሲል ከነማ የ 2-0 ሽንፈት ያስተናገዱ ሲሆን የውድድር ዓመቱን መጥፎ በሚባል መልኩ ጅማሯቸውን እያደረጉ ይገኛል። በዛሬው ጨዋታ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማሳካት ቡድኑ ጋር የሚታየውን ትልቁን የመከላከል ችግር አስተካክለው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል።
በዘንድሮው የውድድር ዘመን በፊት የነበራቸውን መጠሪያ ስማቸውን ቀይረው ወደ ውድድር የቀረቡት ምድረ ገነት ሽረዎች በመጀመሪያው ሳምንት ላይ ያገኙትን ጣፋጭ ድል በሁለተኛው ሳምንት ማሳካት ያልቻሉ እና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር 0-0 የተለያዩ ሲሆን ያንን የአሸናፊነት ስሜት ለመቀየር ቢጫ ለባሾች ጋር ቀላል የማይባሉ ፉክክሮች እንደሚኖሩ ይጠበቃል።
ምድረ ገነት ሽረዎች በዛሬ ጨዋታ ሁሉም የቡድኑ አባላት ዝግጁ ሲሆኑ በወልዋሎ በኩል እንዳልካቸው ጥበቡ እና ኪም ላም ከባለፈው ዓመት በተሻገረ ቅጣት ምክንያት በዛሬ ጨዋታ አይሰለፉም።
ሁለቱ ቡድኖች በፕሪሚየር ሊጉ 4 ጊዜ ተገናኝተው ስሑል ሽረ 2 ጊዜ ድል ማድረግ የቻለ ሲሆን ወልዋሎ 1 አሸንፏል በቀሪው 1 ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል። በአጠቃላይ 7 ጎሎች ሲቆጠሩ ስሑል ሽረ 4 ወልዋሎ ደግሞ ግብ አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው 2012 ጨዋታ አልተካተተም)።

ባህር ዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
በሳምንቱ መርሐግብር ተጠባቂ የሆነው ጨዋታ ከቀኑ 10፡00 ሲል ባህር ዳር ከተማን ከ ኢትዮጵያ ቡና የሚያገናኝ ይሆናል። በሁለተኛው የጨዋታ ሳምንት ከአርባ ምንጭ ከተማ ጋር 1-1 በሆነ ውጤት ነጥብ የተጋሩት የጣና ሞገዶች አራት ነጥብ በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻሉ ሲሆን የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ የሚችሉ ከሆነ በጊዜያዊነት ሊጉን መምራት የሚጀምሩ ይሆናል። በሊጉ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ አዲስ አዳጊውን ነገሌ አርሲን 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ የቻሉት ቡናማዎች በዛሬው ዕለት ከተጋጣሚያቸው ብርቱ የሚባል ፉክክር ይጠብቃቸዋል። ካደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አንዱን ተሸንፈው በአንዱ ድል ያደረጉት ቡናማዎቹ የዛሬውን ጨዋታ ድል በማድረግ ደረጃቸውን ከመሪዎች ተርታ ለማሰለፍ ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በባህር ዳር ከተማ በኩል በባለፈው ጨዋታ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተው ግርማ ዲሳሳ በቅጣት እንዲሁም ክንዱ ባየልኝ በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ በኢትዮጵያ ቡና በኩል መሐመድ ሻባን ፣ ዲቫይን ዋቹኩዋ እና አላዛር ሳሙኤል በጉዳት እንዲሁም ግብ ጠባቂው ዳንላድ ኢብራሂም በቅጣት ምክንያት የዛሬው ጨዋታ ያልፋቸዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ12 ጊዜያት ተገናኝተው ባህር ዳር ከተማ 5 ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 2 ጊዜ ድል ሲያደርጉ አምስቱ ጨዋታዎች አቻ የተጠናቀቁ ናቸው። በግንኙነታቸውም ባህር ዳር ከተማ 21 ኢትዮጵያ ቡና 19 ግቦችን አስቆጥረዋል።
መቻል ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በዚህ የውድድር አመት ሙሉጌታ ምሕረትን የቡድኑ አዲስ ዋና አሰልጣኝ አድርገው የሾሙት መቻሎች በሁለተኛው የጨዋታ ሳምንት ከ መቀለ 70 እንደርታ ጋር 2-2 በሆነ ውጤት የተለያዩ ሲሆን በአንደኛው ሳምንት ያሳኩትን ድል ለመድገም ያሉባቸውን ስህተቶች አስተካክለው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል። በአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ እየተመሩ ያደረጓቸውን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ የተጋሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የመጀመሪያ ሶስት ነጥባቸውን ለማሳካት ከመቻል ጋር ብርቱ ፉክክር የሚጠብቃቸው ይሆናል።
በመቻል በኩል ሁሉም የቡድኑ ሰራዊት ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆኑ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ዘላለም አበበ እና ናትናኤል ዳንኤል ወደ ልምምድ ቢመለሱም ለዛሬው ጨዋታ የመሰለፋቸው ነገር በአሰልጣኙ ዉሳኔ የሚጠበቅ ሲሆን ሌሎች የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ29 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን መቻል 10 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። ባንክ 5 ጊዜ ሲያሸንፍ 14 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። መቻል 38 ሲያስቆጥር ባንክ 31 አስቆጥሯል።

