በጊዜያዊ አሰልጣኞች ሲሰለጥኑ የቆዮት የጦና ንቦቹ አዲስ አለቃ ለማግኘት ከጫፍ ደርሰዋል።
የተቀዛቀዘ የውድድር ዓመት ጅማሮ ያደረገው ወላይታ ድቻ በቅርቡ ከአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ጋር ከተለያየ በኋላ በቴዎድሮስ ቀነኒ እና አምጣቸው ኃይሌ በጊዜያዊ አሰልጣኞች ሲመራ መቆየቱ ይታወሳል።

የክለቡ ቦርድ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ከሰሞኑን ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን በመጨረሻም አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን ለመቅጠር ከውሳኔ እንደደረሰ ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች። የመጀመርያ ድርድሮችን ከአሰልጣኝ መሳይ ጋር በተሳካ ሁኔታ ማድረጋቸውን ሲሰማ በቀጣዮቹ ሁለት ወይም ሦስት ቀናት የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በቀር ድርድሩን በወረቀት ለመጨረስ እና ቡድኑን እንዲረከቡ ለማድረግ መታሰቡን ከውስጥ ምንጮቻችን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
መሳይ ተፈሪ በአሰልጣኝነት ዘመኑ ወላይታ ድቻን ከታችኛው እርከን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንዲገባ በማድረግ በነበረው የስምንት ዓመት ቆይታው ሁሌም በወላይታ ድቻ ደጋፊዎች እና ማኀበረሰብ ዘንድ ትልቅ ስም ተክለው ያለፉ መሆናቸው የማይዘነጋ ሲሆን ፋሲል ከነማ ፣ አርባምንጭ ከነማን እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምክትል እና በዋና አሰልጣኝነት ማገልገላቸው ይታወቃል።

አሰልጣኝ መሳይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የቀራቸው የጥቂት ወራ ኮንትራትን በስምምነት ከተለያዩ በኋላ አሁን ደግሞ ዳግም ከስምትት ዓመት ቆይታ በኋላ በድጋሚ ወደ ቀድሞ ቤታቸው የሚመለሱ ይሆናል።

