በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ ከመመራት ተነስተው ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሰዋል።
ወላይታ ድቻ ከ ሸገር ከተማ
ዘጠኝ ሰዓት ላይ ጅማሮውን ባደረገው ጨዋታ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በፈጣን ሽግግሮች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉትን ወላይታ ድቻዎች ብልጫ የታየበት ነበር። በአመዛኙ
ወጣቱ ቅዱስ ቂርቆስ በተሰለፈበት መስመር ያመዘነ የማጥቃት አጨዋወት የነበረው ቡድኑ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል መድረስ የቻለ ሲሆን በ21ኛው ደቂቃ ተከላካዩ ናትናኤል ናሴሮ የሸገር ከተማን ተከላካዮች አታሎ በማለፍ ሞክሮት ባህሩ ነጋሽ የመለሰው ኳስም ተጠቃሽ ሙከራ ነው።
ከቀዝቃዛው አጀማመር አገግመው ከአጋማሹ አካፋይ በኋላ ጥሩ መነቃቃት በማሳየት የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ሸገር ከተማዎች በ26ኛው ደቂቃ ላይ ሙአዝ ጋሊ ከቆመ ኳስ መቷት የግቡ አግዳሚ ጨርፋ በመወጣችው ሙከራ ቀዳሚ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በ40ኛው ደቂቃም ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በሙአዝ ጋሊ ግሩም ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል፤ ሸገር ከተማዎች ጀቤሳ ሚኤሳ መሬት ለመሬት አሻግሯት ሙአዝ ጋሊ ከሳጥን ውጭ አክርሮ ባስቆጠራት ግሩም ግብ እየመሩ አጋማሹን አጠናቀዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ተሻሽለው የቀረቡት የጦና ንቦች ከአጋማሹ ጅማሮ አስር ደቂቃዎች በኋላ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ቴዎድሮስ ታፈሰ ከያሬድ ዳርዛ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ከሳጥን ውጭ መሬት ለመሬት አክርሮ ያስቆጠራት ግብም የጣና ንቦቹን ወደ ጨዋታ መልሳለች። ከግቡ በኋላም ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በ66ኛው ደቂቃ ሳጥን ውስጥ ዮናታን ኤልያስ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙት ፍፁም ቅጣት ምት በመልካሙ ቦጋለ አማካኝነት አስቆጥረው መሪ መሆን ችለዋል።
የጦና ንቦቹ መሪ ከሆኑበት ግብ በኋላም ካቆሙበት ነበር የቀጠሉት፤ በ74 ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉቀን አዲሱ ከጥሩ የቅብብል ሂደት በኋላ ያገኛትን ኳስ ሳጥን ውስጥ ለነበረው ኪዳኔ አሰፋ ካቀበለው በኋላ አማካዩ ተረጋግቶ ከመረብ ጋር ያዋሃዳት ኳስም የቡድኑን መሪነት አጠናክራለች። ጨዋታው 3ለ1 ከሆነ በኋላም በፈጣን ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ቀጥሎ ሁለቱም ቡድኖች ተጨማሪ ግቦችን ለማግኘት እጅጉን ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በወላይታ ድቻዎች አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን
በሙከራዎች የታጀበ አጀማመር የነበረው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኖች በአለን ካይዋ አማክኝነት ፈጣን ሙከራ ካደረጉ በኋላ በደቂቃዎች ልዩነት ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል።3ኛው ደቂቃ ላይ አለን ካይዋ አክርሮ መቷት ሰይድ ሀብታሙ ከመለሳት በኋላ አማኑኤል ኤርቦ የተመለሰችውን ኳሱ ተጠቅሞ ያስቆጠራት ግብም ኢትዮጵያ መድንን መሪ ማድረግ ችላለች።
ከግቡ በኋላ በሀይቆቹ በኩል ጌታነህ ከበደ መቷት
የግቡ አግዳሚ የመለሳት ኳስ እንዲሁም በኢትዮጵያ መድን በኩል ዳዊት አውላቸው ሞክሯት ሰይድ ሀብታሙ እንደምንም ጨርፎ ያወጣት ሙከራ ተጠቃሾች ናቸው። በ21ኛው ደቂቃም የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጥረት በማድረግ ላይ የነበሩት ሐይቆቹ በጌታነህ ከበደ ግብ አማካኝነት አቻ መሆን ችለዋል። ቢኒያም በላይ ከመስመር ወደ ሳጥን ያሻማት ኳስ ሽመልስ በቀለ በፍጥነት ደርሶ ካሻገራት በኋላ ጌታነህ ከበደ ጨርፎ ከመረብ ጋር ያዋሀዳት ኳስም ቡድኑን አቻ ማድረግ የቻለች ግብ ነች። ሀይቆቹ አቻ ከሆኑበት ግብ በኋላም በጌታነህ ከበደ እና ቢኒያም በላይ አማካኝነት ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ፋሲል ገብረሚካኤል በግሩም ሁኔታ መልሶባቸዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሀይቆቹ ባደረጉት ፈጣን ምላሽ ነበር የጀመረው፤ በ46ኛው ደቂቃ ላይም በያሬድ ብሩክ ፈጣን ግብ መሪ መሆን ችለዋል። ጌታነህ ከበደ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለማራቅ ጥረት ሲያደርግ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ አክርሮ መቷት ተከላካዮች ከመለሷት በኋላ ብሩክ ያሬድ በግሩም ሁኔታ በመምታት መረብ ላይ ያሳረፋት ግብም ሀዋሳዎችን መሪ ማድረግ ችላለች።
ከግቡ መቆጠር በኋላ በነበሩ ደቂቃዎች ሀዋሳ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻለ ብልጫ የነበራቸው ሲሆን ኢትዮጵያ መድን በበኩላቸው ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት የተቃረቡባቸውን ሙከራዎች አድርገዋል፤ በተለይም ረመዳን የሱፍ ከርቀት አክርሮ ያደረጋቸውና በሰይድ ሀብታሙ ጥሩ ብቃት የተመለሱት ኳሶች መድኖችን አቻ ለማድረግ ተቃርበው ነበር። ጥሩ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታም ሀዋሳ ከተማ ከመመራት ተነስቶ ወሳኝ ድል ማስመዝገብ ችሏል።


