ሪፖርት | በአዲስ አበባ ስታዲየም የተከናወኑ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀቁ

ሪፖርት | በአዲስ አበባ ስታዲየም የተከናወኑ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀቁ

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ ከ አዳማ ከተማ እንዲሁም መቻል ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ የወሰዱበት የመጀመርያው አጋማሽ ብርቱ ፉክክር የተካሄደበት ቢሆንም ጥራት ባላቸው ሙከራዎች የታጀበ አልነበረም። በአዳማ ከተማ በኩል በጨዋታው ጅማሮ ነቢል ኑሪ በረጅሙ የተሻገረችውን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ደግሞ ወደ ሳጥን ተሻምታ አብዲሳ ጀማል  ያልተጠቀመባት ዕድልም ተጠቃሾች ናቸው።

በ27ኛው ደቂቃም ጀሚል ያዕቆብ ከመስመር አሻግሯት በሳጥኑ ጠርዝ የነበረው ያሬድ ታደሰ አክርሮ በመምታት ከመረብ ጋር ባዋሃዳት ግብ ብርቱካናማዎቹ መሪ መሆን ችለዋል። ሆኖም መሪነታቸው የዘለቀው ለደቂቃዎች ብቻ ነበር። በ30ኛው ደቂቃ ማይክል ኪፕሩቪ ከብዙዓየሁ ሰይፉ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ የመታትን ኳስ አብዩ ካሳዬ ካዳናት በኋላ ነቢል ኑሪ የተመለሰችውን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም አዳማዎችን አቻ ያደረገች ግብ ነበረች።

ድሬዳዋ ከተማዎች የተሻለ ብልጫ የወሰዱበት ሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። ብዙዓየሁ ሰይፉ በጥሩ መንገድ ወደ ሳጥን ያሾለካትን ኳስ ተጠቅሞ ማይክል ኪፕሩቪ ያደረጋት ሙከራ በአዳማ ከተማ በኩል አቤል ነጋሽ ጥሩ እንቅስቃሴ ስያደርግ ከነበረው መሐመድኑር ናስር የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ጥሩ ሙከራም በብርቱካናማዎቹ በኩል የተደረጉ ሙከራዎች ናቸው።

ከአጋማሹ አካፋይ ደቂቃ በኋላ ብልጫ የነበራቸው ብርቱካናማዎቹ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። መሐመድኑር ናስር ሳጥኑ ጠርዝ ላይ ለነበረው ግሩም መኩርያ አቀብሎት ግሩም አክርሮ መቷት አላዛር ማርቆስ የመለሳት ኳስ እንዲሁም ያሬድ ታደሰ ከመስመር ተሻምታ ተከላካዮች የጨረፏትን ኳስ አክርሮ መቶ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ሙከራም የማታ ማታ ብርቱካናማዎቹን ባለ ድል ለማድረግ የተቃረቡ ወርቃማ አጋጣሚዎች ነበሩ። ጨዋታውም በመጀመርያው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

መቻል ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ከሳምንቱ ተጠባቂ መርሐግብሮች መካከል በነበረው ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የተደረገበት ቢሆንም ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች በማድረግ በኩል የተሻሉ ነበሩ።

በረከት ወልደዮሐንስ ከማዕዝን የተሻማችውን ኳስ ተጠቅሞ በግምባር ገጭቷት ቸርነት ጉግሳ ከመስመር የመለሳት ኳስ እንዲሁም አሸናፊ ጥሩነህ እና ኢዮብ ገብረማርያም ከርቀት አክርረው በመምታት ያደረጓቸው ሙከራዎችም ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ። ሀሰን ሑሴን ከሳጥኑ የግራ ክፍል አክርሮ መቷት ምንታምር መለሰ በግሩም ሁኔታ የመለሳት ኳስም ተጠቃሽ ናት።

ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ሙከራዎችን ሳያደርጉ የቆዩት መቻሎችም በሁለት አጋጣሚዎች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። አብዱልከሪም ወርቁ ከእጅ ውርወራ የተቀበላትን ኳስ በጥሩ መንገድ ተጫዋች አልፎ መቷት የሱፍ ሞሩ በጥሩ ብቃት ወደ ውጭ ያወጣት እንዲሁም ቻላቸው መንበሩ ከቀኝ መስመር አሻምቷት በረከት ደስታ የሞከራት ኳስም ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ናቸው።

 

ሁለተኛው አጋማሽ ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ የተደረገበት እንዲሁም ጥቂት የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበት ነበር። ለግብ የቀረበ ሙከራ በማድረግ ረገድ የተሻሉ በነበሩት መቻሎች በኩል ዮሴፍ ታረቀኝ ሳጥን ውስጥ በራሱ ጥረት ያገኛትን ኳስ በጥሩ መንገድ ዞሮ የሞክራት ዒላማዋን ያልጠበቀች ሙከራ እንዲሁም መሐመድ አበራ ከቀኝ መስመር ገፍቶ መቷት የሱፍ ሞሩ የመለሳት ኳስ በአጋማሹ የታዩ የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ። በኤሌክትሪክ በኩልም አብዱልመጅድ ሁሴን እና በፍቃዱ አስረሳኸኝ ከርቀት ያደረጓቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታም ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።