ሪፖርት | በአዳማ የተደረጉ ጨዋታዎች አቻ ተጠናቅቀዋል

ሪፖርት | በአዳማ የተደረጉ ጨዋታዎች አቻ ተጠናቅቀዋል

በሳምንቱ በመጀመሪያ ቀን በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ 1ለ1 ሲለያዩ የአርባምንጭ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቅቋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ

እምብዛም የግብ ማግባት ሙከራዎች ባልተስተዋሉበት በእለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ጥረቶችን ያሳዩ ቢሆንም ሦስተኛው ሜዳ ክፍል ላይ ደርሰው አደጋ የፈጠረ የጠራ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በአንፃራዊነት ወደ ፊት በመሄድ አኳያ የተሻሉ የነበሩት ፈረሰኞቹ ምንም እንኳን ብልጫ ያግኙ እንጂ አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ በአጋማሹ ሲያደርጉ ባንመለከትም 33ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ አቤል ያለው በግንባሩ ጨርፎ የተሻገረውን ኳስ ሀብታሙ ጉልላት አክርሮ የመታውን ኳስ የወላይታ ድቻ ተከለካዮች እንዴትም ተደራርበው ያገዱባቸው ጠንካራው ሙከራ ተጠቃሽ ነበር ። የጦና ንቦችም እንዲሁ ከተጋጣሚው ቡድን ተመሳሳይ የሆነ እንቅስቃሴ እያደረጉ የቆዩ ቢሆንም በአመዛኙ የኳስ ንክኪ ብልጫ ተወስዶባቸው ሰንብተው በመጀመሪያ ዒላማውን በጠበቀ ሙከራ መሪ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ተመስገን ዮሐንስ ኳስ በሳጥኑ ጠርዝ ላይ ለነበረው ብርሃኑ አሻሞ ሲያቃብል ኳሱን የነጠቀው ቴዎድሮስ ኃይለማርያም በስህተቱ መነሻነት የተገኘውን ኳስ 40ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ ሆኖ መሬት ለመሬት በመምታት ማስቆጠር ችሏል። ግብ ካስቆጠሩ በኋላ የተነቃቁት የጦና ንቦች አጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ ተጨማሪ ግብ ለመሆን የቀረበ አጋጣሚ አግኝተው የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀሙበት ቀርተው የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።

ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲመለስ በይበልጥ ጠንከር ብለው የተመለሱት ፈረሰኞቹ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብሎም የግብ ማግባት እድሎችን እየፈጠሩ ቆይተው ጨዋታው 67ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የአቻነት ግብ ማግኘት ችለዋል። ተቀይሮ ገብቶ የጨዋታውን ሂደት ከመቀየር ባሻገር ረጃጅም ኳሶችን እየጣለ የነበረው ፉዓድ አብደላ ከራሳቸው ሜዳ ክፍል ከተከላካይ ጀርባ የጣለውን ኳስ አቤል ያለው ፍጥነቱን ተጠቅሞ ደርሶ በጥሩ እይታ አስቆጥሮ ወደ ጨዋታ መልሷቸዋል።

ከግቡ በኋላም ጥንካሬያቸውን አስቀጥለው በጫና ወደፊት የሄዱ የነበሩት ፈረሰኞቹ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር አብዝተው በመጣር ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን የፈጠሩ ቢሆንም እድሎቹን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። የጦና ንቦችም ቀዝቀዝ ብለው በቀጠሉበት በሁለተኛው አጋማሽ ብዙም የግብ እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ የቀሩ ቢሆንም 76ኛው ደቂቃ ላይ ኪዳኔ አሰፋ ብቻውን ሆኖ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ያመከነው አስቆጪው አጋጣሚ ይጠቀሳል። ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

አዞዎቹን ከሐይቆቹ ያገናኘው ሁለተኛው ጨዋታ ቀዝቃዛ ፉክክር እያስመለከተን ጅማሮውን ሲያደርግ በሂደት ከደቂቃ ደቂቃ ወደ ፊት በመጠጋት እድሎችን ሲፈጥሩ የነበሩት አዞዎቹ የተሻለ እንዲሁም ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን አድርገዋል። እምብዛም ወደ ሦስተኛው ሜዳ ክፍል መድረስ ያልቻሉት ሐይቆቹ ሽመልስ በቀለ ሳጥን ውስጥ አግኝቶ ለመምታት ከዘገየበት አጋጣሚ ውጪ የጠራ አጋጣሚ እንኳን ለማድረግ የተቸገሩበትን አጋማሽ ሲያሳልፉ አስተውለናል።

እድሎችን በመፈጠር ረገድ በአጋማሹ የተሻሉ የነበሩት አዞዎቹ በፍቅር ግዛው በመስመር በኩል ኳስ ይዞ ገብቶ ሳጥን ውስጥ ለይገዙ ቦጋለ ያሻገረውን ኳስ ፍቃደሥላሴ ከእግሩ ስር ተንሸራቶ ጨርፎ አውጥቶባቸው የማዕዘን ምት አግኝቶ የተሻማውን ኳስ አሸናፊ ፊዳ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን የመጀመሪያውን ጠንካራ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሰይድ ሀብታሙ እንዴትም ጨርፎ አውጥቶባቸዋል።

የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉት አዞዎቹ አጋማሹ ሊጠናቀቅ ጭማሪ በታየው ደቂቃ ላይ በረከት ሳሙኤል ይገዙ ቦጋለ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ኳስ ፀጋዬ አበራ አክርሮ መትቶ ያደረገውን ሙከራ የግቡ አግዳሚ ባይመልስበት አጋማሹን እየመሩ ወደ እረፍት ለማምራት ተቃርበው የነበረ ሲሆን አጋማሹም ቀዝቃዛውን የሀዋሳ ከተማን የማጥቃት እንቅሰቃሴ አስመልክቶን ጥቂትም ቢሆንም የአርባምንጭ ከተማዎችን የግብ ማግባት ጥረቶችን አስመልክቶን ተገባዶ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት ከጨዋታው ጋር ጫና ፈጥረው በመጫወት የተመለሱት ሐይቆቹ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የጨዋታ ብልጫ እንዲሁም በመጀመሪያው አጋማሽ የታየባቸውን ወደፊት የመሄድ ችግር ቀርፈው ቀዳሚ ለመሆን አጨዋወታቸውን ሶስተኛው ሜዳ ክፍል እያደረጉ ነገር ግን ጠንከር ያለ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ይሰንብቱ እንጂ ጌታነህ ከበደ ሳጥን ውስጥ ሆኖ የመታት ኳስ ከግቡ ቋሚ ብረት ታካ ከወጣች በኋላ ሌላ ሙከራ መመለከት አልቻልንም።

በመልሶ ማጥቃት እንዲሁም በረጃጅም ኳሶች የተቃራኒ ቡድን ሜዳ ክፍል ሲደርሱ የነበሩት አዞዎች በተለይም በፍቅር ግዛው ከይገዙ ቦጋለ ጋር ባደረጉት ጥሩ ጥምረት 64ኛው ደቂቃ ላይ በፍቅር ግዛው በግሩም መጀመሪያ ደረት ንክኪ ኳስ ይዝ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው እንዴትም ያገደበት እንዲሁም የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ተቀይሮ  ሜዳ የገባው የአዞዎቹ ተጫዋች አሸናፊ ተገኝ ከግራ መስመር በኩል ኳስ ይዞ ወደ ሳጥን ሲያሻማ ኳሱ ተቆርጦ ወደግብነት ለመቀየር ጥቂት ሲቀረው ተዘናግቶ የነበረው ሰይድ ሐብታሙ እንዴትም ተንጠራርቶ ኳሱን ባያግድባቸው ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ባለቀ ደቂቃ ግብ ለማግኘት የተቃረቡበት ያልተጠበቀ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው ያለ ግብ ተጠናቋል።