ሪፖርት | አዳማ እና ሀዋሳ ጣፋጭ ድሎችን ተጎናፅፈዋል

ሪፖርት | አዳማ እና ሀዋሳ ጣፋጭ ድሎችን ተጎናፅፈዋል

በአ/ሳ/ቴ/ዩ በተደረጉት እና ሰባት ግቦችን ባስመለከቱን የዕለቱ ጨዋታዎች አዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ አዳማ ከተማ

በአጋማሹ የመጀመሪያ ደቂቃዎች እጅጉን ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት የአዳማ ከተማዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል እየደረሱ የግብ አደጋዎችን መፍጠር ቢችሉም በ20ኛው ደቂቃ ላይ ያልተጠበቀ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። የአዳማ ተከላካዮች በሰሩት የቅንጅት ስህተት ብሩክ ብፁአምላክ ኳስ በመንጠቅ የሰጠውን ኳስ አዲስ ግደይ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ያልተጠበቀ ግብ ያስተናገዱት አዳማ ከተማዎች ስህተታቸውን ለማረም እንዲሁም ምላሽ ለመስጠት ሁለት ደቂቃ ብቻ ነበር የወሰደባቸው። በ22ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም መሐመድ ከመስመር ያቀበለውን ኳስ ቢኒያም ዐይተን በድንቅ ብቃት ሁለት የባንክ ተከላካዮችን በማለፍ ኳስና መረብን ድንቅ በሆነ አጨራረስ አገናኝቶ ቡድኑን አቻ አድርጓል።

የአቻነት ግብ ካገኙ በኋላ ይበልጥ መሪ መሆን የሚችሉበትን ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት አዳማ ከተማዎች በ37ኛው ደቂቃ ላይ ያሲን ጀማል አብዱልከሪም መሐመድ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን የፍጹም ቅጣት ምት አህመድ ሁሴን ወደ ግብነት ቀይሮ አዳማን ከመመራት ተነስተው መሪ ማድረግ አስችሏል።

የአጋማሹ መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ በአዳማ በኩል አህመድ ሁሴን በግንባር ገጭቶ ሞክሮት የግቡ ቋሚ የመለሰበት እንዲሁም በንግድ ባንኮች ዘላለም አበበ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ሳንመለከት የመጀመሪያው አጋማሽ በአዳማ 2-1 መሪነት ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ የተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ የቀረቡት ንግድ ባንኮች በ50ኛው ደቂቃ ላይ መነሻውን ከቅጣት ምት  ያደረገውን እና በዘላለም አበበ በግንባር ተገጭቶ  የደረሰውን ኳስ ሳይመን ፒተር በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ንግድ ባንክን ወደ ጨዋታው መልሷል።

በግቦች ታጅቦ መካሄዱን የቀጠለው ጨዋታ በ64ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማው ሳሙኤል ዮሐንስ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ አቡበከር ሳኒ በግንባሩ በመግጨት ግብ አስቆጥሮ ያጡትን መሪነት ዳግመኛ እንዲያገኙ አድርጓል። እጅግ አስደሳች የነበረው እና ተመልካችን ቁጭ ብድግ ያደረገው ሳቢ እና አስደሳች ጨዋታም በአዳማ ከተማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ነጌሌ አርሲ

በአንድ ነጥብ ተለያይተው 2ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ በመሆን ጨዋታቸውን ያደረጉት ሁለቱ ቡድኖች በኳስ እንቅስቃሴ ረገድ ተቀራራቢ የሚባል ብልጫ ቢኖራቸውም ወደ ግብ ደጋግሞ በመድረስ ረገድ ነጌሌ አርሲዎች የተሻሉ ነበሩ። ገብረመስቀል ዱባለ ወደ ግብ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂውን አልፎ የግቡን መረብ ይነካል ተብሎ የተጠበቀውን ኳስ ወንድምአገኝ  ማዕረግ ከመስመር ኳሷን አውጥቶ ለሀዋሳዎች የልብ ምት ነፍስ ዘርቶበታል።

ግብ በማስቆጠር ረገድ ሀዋሳ ከተማዎች ቀዳሚ ነበሩ። በ12ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ሽመልስ በቀለ ወደ ግብነት በመቀየር ሀዋሳን መሪ አድርጓል።

ከዕረፍት መልስ የተወሰደባቸውን ብልጫ ለማስመለስ ተጠናክረው ወደ ሜዳ የገቡት ነጌሌ አርሲዎች የመስመር አጥቂዎቻቸውን ዒላማ ያደረጉ የማጥቃት ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በ79ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳ ከተማዎች የነጌሌ ጥረት ላይ ውሃ የቸለሰ ግብ አስቆጥረዋል። ተቀይሮ ከገባ 50 ያክል ሰከንዶችን ብቻ ያስቆጠረው ተባረክ ሄፋሞ ከጌታነህ ከበደ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ የሀዋሳን የአሸናፊነት ጉዞ ያረጋገጠ ግብ አስቆጥሯል።

በጨዋታው መገባደጃ ላይ ነጌሌዎች ጫና ፈጥረው ግብ ለማግኘት በአለኝታ ማርቆስ እና ሮሆቦት ሰላሎ አማካኝነት ለግብ የቀረበ ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው 2-0 በሆነ ውጤት ሽንፈትን አስተናግደዋል። ይህንንም ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የቀረውን ፋሲል ከነማ እና የዛሬ ተጋጣሚውን አርሲ ነገሌን በመብለጥ 2ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።