በጨዋታ ሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን አዲስ አበባ ላይ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ወልዋሎ ሀዲያን ሲያሸንፍ በአምስት ግቦች የታጀበው የአርባምንጭ እና የፋሲል ጨዋታ በዐፄዎቹ 3ለ2 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ
የጨዋታ ሳምንቱ ቀዳሚ ጨዋታ ቀን 7 ሰዓት ሲል ሀዲያ ሆሳዕናን ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ አገናኝቷል። የነብሮቹን ፈጣን ሽግግር ባስተዋልንበት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ፍፁም ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ የቻሉ ሲሆን በተለይም ገና የጨዋታ ጅማሮ ላይ የመጀመሪያ ደቂቃ ሳይጠናቀቅ ብሩክ በየነ በመስመር በኩል ኳሷን አግኝቶ ተከላካዮችን በቀላሉ ቀንሶ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠብቅ ኳሷ ከፍ ብላ የወጣችበት አስቆጪዋ አጋጣሚ ትጠቀሳለች። እንዲሁም 15ኛው ደቂቃ ላይ ጠንከር ያለ ሙከራ ተመስገን ብርሃኑ ከቀኝ መስመር በኩል ያሻገራትን ኳስ ያገኘው ፀጋአብ ግዛው አክርሮ ሲመታት ግብ ጠባቂው እንዴትም ባያግድባቸው ቀዳሚ ግብ አስቆጣሪ ለመሆን የቀረቡበት አጋጣሚ ነበር።

መዳረሻቸውን ቁመታሙ የፊት መስመር ተጫዋች ሀፊዝ ኮንኮኒ ላይ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶችን ወደ ሳጥን ሲጥሉ የነበሩት ቢጫ ለባሾቹ በአጋማሹ ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች በማድረግ ረገድ ቀዳሚ ነበሩ። በዚህም 6ኛው ደቂቃ ላይ ሀፊዝ ኮንኮኒ ያደረገው ሙከራ ሲጠቀስ ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ 21ኛው ደቂቃ ላይ ማግኘት ችለዋል። ግብ ጠባቂው በረጅሙ ያሻገራትን ኳስ ዳዊት ገብሩ በግንባሩ ገጭቶ ሲያመቻችለት እንዳልካቸው ጥበቡ በግሩም ንክኪ ኳሷን ተቆጣጥሮ ተረጋግቶ ወደ ግብነት ቀይሯታል። በዚህ ብቻ ያላበቁት ቢጫ ለባሾቹ 36ኛው ደቂቃ ላይ በሀፊዝ ኮንኮኒ አማካኝነት ተጨማሪ ግብ ለመሆን የቀረበ አደገኛ ሙከራ አድርገው ግብ ጠባቂው አግዶባቸዋል። ከግቡ መቆጠር በኋላም ሀዲያ ሆሳዕናዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በአመዛኙ ወስደው የአቻነት ግብ ፍለጋቸውን የቀጠሉ ቢሆንም አጋማሹ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በቢጫ ለባሾቹ 1ለ0 መሪነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።
ከዕረፍት መልስ ጠንከር ብለው የተመለሱት ነብሮቹ ወደ ጨዋታ ለመመለስ የወደፊት የመሄድ እንቅስቃሴዎች እያደረጉ እየተመለከትን በመልሶ ማጥቃት የተሻለ የግብ ማግባት ሙከራ ማድረግ የቻሉት ቢጫ ለባሾቹ መሪነታቸውን ያጠናከረችውን ግብ አስቆጥረዋል። 63ኛው ደቂቃ ላይ በመስመር በኩል ወደ ሳጥን የተሻገረውን ኳስ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ኤፍሬም ኃይለማርያም በፍጥነት ደርሶ ወደ ግብ ሲመታት ግብ ጠባቂው አግዷት የተመለሰችውን ኳስ ከኋላ ኳሱን ለማገድ እየመጣ ያለው የነብሮቹ ተከላካይ ቃለአብ ውብሸት ባደረጋት ንክኪ ኳሷ በራሳቸው መረብ ላይ ማረፍ ችላለች።

ሳይጠበቅ ግብ አስተናግደው በጫና ወደፊት መግባታቸውን የቀጠሉት ነብሮቹ የተጫዋች ቅያሪ አድርገው ወደ ጨዋታ የመለሰቻቸውን ግብ አግኝተዋል። ተመስገን ብርሃኑ እና ብሩክ በየነ ባደረጉት ጥሩ ንክኪ የተገኘውን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ ሜዳ የገባው ደስታ ዋሚሾ በመጀመሪያ ንክኪ ኳሷን አግኝቷት ሳጥን ውስጥ ይዞ ገብቶ መረብ ላይ እንድታርፍ አድርጓታል። ጨዋታው 2ለ1 ከሆነ በኋላ ነብሮቹ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በሙሉ ኃይላቸው ወደ ተቃራኒ ቡድን ሜዳ ክፍል እየገቡ ጫና ሲያደርጉ ያስተዋልን ሲሆን ቢጫ ለባሾቹ በበኩላቸው ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደኋላ አፈግፍገው በመልሶ ማጥቃት እየገቡ ተጨማሪ ግብ ለመሆን የቀረቡ አስቆጪ አጋጣሚዎችን የጨዋታ መጠናቀቂያ ደቂቃ ድረስ መፍጠር ችለዋል። ሆኖም ግን የነብሮቹን ጫና እና የቢጫ ለባሾቹ መከላከል ጥንካሬ ያስመለከተን ጨዋታው በመጨረሻም 2ለ1 በሆነ ውጤት ለመጠናቀቅ ተገዷል።
አርባምንጭ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ
ሁለት በደረጃ ሰንጠረዡ ተቃራኒ ቦታ ላይ የሚገኙ ቡድኖችን ያገናኘው የእለቱ ሁለተኛ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማን ከፋሲል ከነማ አገናኝቷል። በፈጣን አጀማመር የግብ ፍለጋ ያደረጉት ዐፄዎቹ በጥሩ ተነሳሽነት ወደፊት እየሄዱ ቆይተው ከአስራ ሁለት ደቂቃ ጥበቃ በኋላ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። በጥሩ ኳስ ቅብልል ሳጥኑ ጋር ደርሰው ዳግም አወቀ የጣላትን ኳስ ያገኘው ቃልኪዳን ዘላለም በግሩም ሁኔታ ኳሷ አየር ላይ እንዳለች አክርሮ መቷት መረብ ላይ እንድታርፍ አድርጓታል።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደፊት የመሄድ ብልጫ የነበራቸው አዞዎቹ 17ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ ተገኝ ያመቻቻትን ኳስ ፈሊፕ ጄሮም ከሳጥን ውጪ ሆኖ መሬት ለመሬት መቷት ግብ ጠባቂው ባያግድባቸው አቻ ለመሆን የቀረቡበት የመጀመርያ አደገኛ ሙከራ ካደረጉ በኋላ 24ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ከራሳቸው ሜዳ ከተከላካዮች ጀርባ የተጣለችውን ኳስ ታምራት ኢያሱ ጉልበቱን እና ፍጥነቱን ተጠቅሞ ተከላካዮችን በማለፍ በብልሃት አስቆጥሯት አቻ አድርጓቸዋል።

ከአቻነት ግብ መቆጠር በኋላ ዐፄዎቹ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ ስንመለከት አዞዎቹ ደግሞ በአንፃራዊነት መሪ ለመሆን በጫና ሶስተኛው ሜዳ ክፍል እየደረሱ ጨዋታው 33ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ዐፄዎቹ መሪነታቸውን ዳግም መረከብ የቻሉበትን አጨቃጫቂ ግብ አስቆጥረዋል። በረጅሙ ተጥሎ ተጨራርፋ የተገኘችውን ኳስ ያገኘው ያሬድ ብርሃኑ ያሻገራትን ኳስ ቃልኪዳን ዘላለም በእጁ ሲያስቆጥራት የአዞዎቹ ተጫዋቾች በእጅ ነው ያስቆጠረው በሚል ቅሬታ ቢያቀርቡም የእለቱ ዋና ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ግቧን አፅድቋታል። በፈጥን ሽግግሮች ታጅቦ ተጨማሪ ግቦች ሊስተናገዱ የቀረቡበት ጥሩ ፉክክር ያስመለከተን የመጀመሪያው አጋማሽ ሶስት ግቦች ተቆጥሮበት ተገባዶ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።
ከመልበሻ ክፍል መልስ በጣን ማጥቃት እንቅስቃሴ የተመለሱት አዞዎች ሳጥን ውስጥ ኳስ ይዘው በሚገቡበት ቅፅበት ታምራት ኢያሱ ላይ ምኞት ደበበ በሠራው ጥፋት ፍፁም ቅጣም ምት አግኝተው ፀጋዬ አበራ ወደ ግብነት ቀይሮ አቻ መሆን ችለዋል። ይሁን እንጂ በአንድ ደቂቃ ልዩነት አፄዎቹ ዳግም መሪነት የተረከቡበት ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። ከቅጣት ምት የተገኘውን ኳስ ሀብታሙ ተከስተ ቶሎ መሬት ለመሬት አስጀምሮ ያሻገራትን ኳስ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በፍጥነት ደርሶ በቀላል ንክኪ መረብ ላይ አሳርፏታል።

አዞዎቹ የአቻነት ግብ ፍለጋ በሙሉ ኃይላቸው ሲያጠቁ እየተመለከትን ዐፄዎቹም ለተጨማሪ ግብ በሚያደርጉት መልሶ ማጥቃት ጨዋታው ግለቱን ጨምሮ ቀጥሎ ዐፄዎቹ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ በማድረግ ረገድ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ 70ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ አግኝቶ ያመከነው እና ዳግም አወቀ መስመር በኩል ኳስ ይዞ ገብቶ መሬት ለመሬት የመታትን ኳስ ግብ ጠባቂው የተቆጣጠረባቸው ሙከራዎች ተጠቃሾች ናቸው።
ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጣት አዞዎቹ በጫና ወደ ተጋጣሚዎቻቸው ሜዳ ክፍል እየደረሱ ተከላካዮችን እየፈተኑ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉ ቢሆንም ዐፄዎቹ ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ተከላካይ መስመራቸውን በማጠናከራቸው ግብ ማስቆጠሩ እንዳሰቡት ሳይሆንላቸው ቀርቶ በግቦች የታጀበው ሁለተኛው ጨዋታ በዐፄዎቹ 3ለ2 በሆነ አሸናፊነት ተቋጭቷል።

