የሲቢኢ የኢትየጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀመሩ፤ ሸገር ከተማን ከ ምድረ ገነት ሽረ እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕናን ከመቻል ያገናኙ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተቋጭተዋል።

ሸገር ከተማ ከ ሽረ ምድረ ገነት
ተመጣጣኝ የሆነ የኳስ ቁጥጥርን ባስመለከተን ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሸገር ከተማዎች በተጋጣሚ ላይ ጫናዎችን በመፍጠር በሚገኙ ስህተቶች ግቦችን ለማግኘት ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም የተነሳ ምድረ ገነት ሽረዎች ኳስን ከራሳቸው የግብ ክልል መስርተው ለመውጣት ሲቸገሩ ተስተውሏል። ይህንንም ተከትሎ ሸገር ከተማዎች ያሬድ መኮንን በ6ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ሪችሞንድ አይ ጨርፎ በግቡ አግዳሚ ባወጣበት እንዲሁም በድጋሚ 12ኛው ደቂቃ ላይ ከፍ አድርጎ አንስቶ መቶት በግቡ አግዳሚ ለጥቂት በወጣበት ሙከራ ለግብ የቀረቡ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም ግብ ሳይቆጠር አጋማሹ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሸገር ከተማዎች አሁንም ጫናዎችን ፈጥረው መጫወት የቀጠሉ ሲሆን ሸገር ከተማዎች በበኩላቸው ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በቁጥር በዛ ብለው በመከላከል በመልሶ ማጥቃት ግቦችን ለማግኘት ሞክረዋል። ይህንንም ተከትሎ 77ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ማሙሽ ከዳንኤል ዳርጌ የተቀበለው እና የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሁኖ መቶት ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ ቀለል አድርጎ በያዘበት ብቸኛውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ቢያደርጉም በጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ግብ ሳያስመለክቱን ጨዋታው 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከ መቻል
መቻሎች መጠነኛ ብልጫ በወሰዱበት የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግብ የማግባት ፍላጎቶች የተስተዋሉበት ነበር። 9ኛው ደቂቃ ላይ በየአብሥራ ተስፋየ ጠንከር ያለ ምት ሙከራ አድርገው በግቡ አግዳሚ ለጥቂት የወጣባቸው መቻሎች 21ኛው ደቂቃ ላይ መሪ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል። ከሜዳው የቀኝ ክፍል ዓለምብርሃን ይግዛው ያሻማውን ኳስ ግብ ጠባቂው መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ የጨረፈው ሲሆን ይህንንም ዕድል ከጀርባ ሁኖ ያገኘው ቸርነት ጉግሳ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ችሏል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ሀዲያዎች 32ኛው ደቂቃ ላይ መነሻውን ከማዕዘን ምት አድርጎ ተመስገን ብርሃኑ እግር ላይ የደረሰው እና ከሜዳው ጠርዝ ላይ ሁኖ ያቀበለውን ኳስ ያገኘት ደስታ ዋሚሾ በእግሩ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አቻ ያደረገ ግብ አስቆጥሯል። መቻሎች በመሐመድ አበራ ለግብ የቀረበ ሙከራን ቢያደርጉም በግብ ጠባቂው ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ አጋማሹ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ መቻሎች በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም የግብ ሙከራ ሳያስመለክቱን ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን አስቆጥረዋል። ከብዙ ደቂቃዎች መጠበቅ በኋላ በዓለምብርሃን ይግዛው አማካኝነት 81ኛው ደቂቃ ላይ መሬት ለመሬት ሞክሮቶ በግቡ ቋሚ ለጥቂቶ በወጣበት እንዲሁም 84ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂው በመለሰበት ሙከራዎች ግቦችን ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም ጠንካራውን የሀዲያን የመከላከል አጥር ማፍረስ ተስኗቸው፤ በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል::

