ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሲዳማ ቡና ያለግብ ሲለያዩ ሀዋሳዎች አዳማን 2ለ0 በማሸነፍ በግብ ክፍያ ተበልጠው ሁለተኛ ደረጃ መቀመጥ የቻሉበትን ውጤት አስመዝግበዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ሲዳማ ቡና
ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከሲዳማ ቡና ባገናኘው ጨዋታ ሲዳማዎች በመጀመሪያው ጨዋታ ምዕራፍ የተሻለ የጨዋታ እንቅስቃሴ እያደረጉ በአንድ ለአንድ ቅብብል የተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል መድረስ የቻሉ ቢሆንም እንደነበራቸው የጨዋታ ብልጫ የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም። ሀብታሙ ታደሰ ከሳጥን ውጪ መቷት ግብ ጠባቂው የያዘበት ብቸኛው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲጠቀስ ሌሎች ሳጥን ውስጥ የሚፈጠሩ ጥረቶች ጠንካራ ሆኖ በዋለው በኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከላካይ መስመር እየተቋረጠባቸው ተቸግረዋል።
በአጋማሹ ከኳስ ጋር ብዙም ቆይታ ያላደረጉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ በማድረግ ረገድ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን አንዋር በድሩ 20ኛው ደቂቃ ላይ ርቀት ላይ ሆኖ አክርሮ መቷት ግብ ጠባቂው እንዴትም ያወጣባቸው አደገኛው ሙከራ እና 32ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ የማነሀ ከግራ መስመር ወደ ጎል አሻግሯት በግብ ጠባቂው እና በግቡ አግዳሚ ላይ ተጨርፋ የወጣችው ኳስ ተጠቃሾች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች በሙሉ ኃይላቸው እያጠቁ ግቦችን ለማግኘት እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ በቁጥር በርከት ብለው የተቃራኒ ቡድን ሜዳ ክፍል የደረሱ ቢሆንም አጋጣሚዎችን ወደ ግብነት መቀየር ተስኗቸዋል። እንደ መጀመሪያው ጨዋታ ምዕራፍ ሁሉ የተጋጣሚውን ጥቃት እየተከላከሉ በመልሶ ማጥቃት ወደፊት ሄደው እድሎችን መፍጠር የቻሉት ኤሌክትሪኮች ግብ መሆን የሚችሉ አድሎችን የፈጠሩ ቢሆንም ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታው ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።
አዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ
አዳማ ከተማን ከሀዋሳ ያገናኘው የምሽቱ ተጠባቂው ጨዋታ አዳማዎች ገና የጨዋታ ጅማሮ ላይ አቡበከር ሳኒ በመስመር በኩል ኳስ ይዞ ሳጥን ውስጥ ገብቶ በጠባብ አንግል ባደረገው ፈጣን የግብ ማግባት እንቅስቃሴ ጨዋታው ግቦች እንደሚቆጠርበት ፍንጭ ካሳዩ በኋላ በኳስ ቁጥጥርም ብልጫ ወስደው እየተጫወቱ ሳይጠበቅ ግብ አስተናግደዋል። 7ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት ቶማስ ያሻገራት ኳስ ሽመልስ በቀለ በፍጥነት ደርሶ በእርጋታ አስቆጥሯት ሐይቆቹ መሪ አድርጓል።

አዳማ ከተማዎች አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት ፈጣን ሽግግሮች እያደረጉ ወደፊት ሄደው 11ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከቢኒያም ዐይተን የተሻገረለት ኳስ ሳጥን ውስጥ መሬት ለመሬት መቷት ሰይድ ሀብታሙ የያዘባቸውን አደገኛ ሙከራ ካደረጉ በኋላ ሐይቆቹ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ሌላ ግብ አስቆጥረዋል። የመጀመሪያ ግብ አስቆጥረው ከ7 ደቂቃ በኋላ ምንተስኖት ቶማስ እና የአብሥራ ደግፌ ባደረጉት ጥሩ መግባባት በቀኝ መስመር ሆኖ የአብሥራ ያሻገራትን ኳስ ተባረክ ሄፋሞ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር መሪነታቸውን እንዲያጠናክሩ አስችሏቸዋል።

የአዳማ ከተማዎች ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በተመለከትንበት በመጀመሪያው ጨዋታ ምዕራፍ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን ዳዋ ሆቴሳ አሻምቷት ብዙዓየሁ ሰይፉ በግንባሩ ገጭቶ ሰይድ ሀብታሙ የተቆጣጠረባቸው እና አቡበከር ሳኒ ከቀኝ መስመር የተሻገረችውን ኳስ ተንሸራቶ ወደ ግብ መቷት ግብ ጠባቂው መልሷት ራሷን ኳስ ለአቤኔዘር ሲሳይ አመቻችቶለት መሬት ለመሬት መቷት ሰይድ ሀብታሙ ድጋሚ ያመከነባቸው ሙከራዎች ተጠቃሾች ናቸው።
ጨዋታው ከእረፍት ሲመለስ አዳማዎች ካቆሙበት ቀጥለው ቶሎ ቶሎ በፈጣን ሽግግር ሳጥን ውስጥ እየገቡ ወደጨዋታ ለመመለስ ተደጋጋሚ የግብ ማግባት ሙከራዎችን እና አስቆጪ አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል። በተለይም 78ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን ኳስ ይዞ በሚገባበት ቅፅበት ፍቃደሥላሴ ደሳለኝ በሠራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ዳዋ ሆቴሳ መቷት የግቡ ቋሚ መልሶባቸው ወደ ጨዋታው የሚችሉበት አጋጣሚ ተበላሽቶባቸዋል። ሐይቆቹ በበኩላቸው ኳሶችን እያራቁ በመልሶ ማጥቃት 71ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ርቀት ላይ ሆኖ መቷት ግብ ጠባቂው እንዴትም ያዳነባቸው ተጨማሪ ግብ ለመሆን የቀረበ አደገኛ ሙከራ የነበረ ሲሆን በመከላከልም ጥሩ ሆነው አምሽተው ጨዋታውም በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ተጠናቋል።

