ሪፖርት | በሀዋሳ የተካሄዱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀቁ

ሪፖርት | በሀዋሳ የተካሄዱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀቁ

ጥሩ ፉክክር በተደረገባቸው ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ እንዲሁም ሲዳማ ቡና እና ወልዋሎ ነጥብ ተጋርተዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

ሐይቆቹ እና ብርቱካናማዎቹን ያፋለመው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመሪያው በሙከራዎች የታጀበ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ነበር። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ ብልጫ የነበራቸው ሀዋሳ ከተማዎች ምንተስኖት ቶማስ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቶት ወደ ውጭ በወጣው እንዲሁም  ጌታነህ ከበደ በጥሩ መንገድ አሻግሯት ተባረክ ሄፋሞ በደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ባልተጠቀመባትና ፍሬው ጌታሁን ባዳናት ወርቃማ ዕድል መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ሐይቆቹ የተሻለ ጫና ፈጥረው ጨዋታውን ቢጀምሩም ግብ በማስቆጠር ረገድ ቀዳሚ የነበሩት ግን ብርቱካናማዎቹ ነበሩ፤ ድልአዲስ ገብሬ ከቀኝ መስመር ተሻምታ የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች የመለሷትን ኳስ ተጠቅሞ ከሳጥን ውጭ በግሩም ሁኔታ ያስቆጠራት ግብም ድሬዳዋ ከተማን መሪ ማድረግ የቻለች ግብ ነች።

 

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ፉክክር ያስመለከተው ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ ድሬዳዋ ከተማዎች በፈጠሩት ጫና ጅማሮን ያደረገ ሲሆን ቡድኑ በሁለት አጋጣሚዎችም መሪ ለመሆን ተቃርቦ ነበር። አብዱሰላም የሱፍ በግራ መስመር በኩል ከቆመ ኳስ በቀጥታ መቷት አግዳሚው የመለሰበት ወርቃማ አጋጣሚ እንዲሁም አብዱሰላም የሱፍ ከግራ መስመር አሻምቷት መሐመድኑር ናስር በግምባሩ ገጭቶ ሰይድ ሀብታሙ የመለሰበት ኳስም ብርቱካናማዎቹን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ናቸው።

አጋማሹ በተቀዛቀዘ ሁኔታ ከጀመሩ በኋላ ያብስራ ደግፌ የግብ ጠባቂው መውጣት አይቶ ከርቀት በሞከራት ኳስ ሙከራ ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎችም በ61ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል፤ ሽመልስ በቀለ ቀደም ብሎ ጥሩ ሙከራ ያደረገው ያብስራ ደግፌ ያሸነፈውን የሰማይ ኳስ አግኝቶ ከመረብ ጋር ያዋሀደው ኳስም ሐይቆቹን ወደ ጨዋታው የመለሰ ግብ ነው። ጨዋታው ከግቡ መቆጠር በኋላም በጥሩ ፉክክር ቢዘልቅም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ሲዳማ ቡና ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

በሰንጠረዡ ሁለት ፅንፍ የሚገኙ ክለቦችን ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥቂት ሙከራዎች የተደረጉበት እንዲሁም ወልዋሎዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉበት ነበር። ኮንኮኒ ሐፍዝ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቶት ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ካል ጨርፎት ቋሚውን ገጭቶ የተመለሰ ኳስም ቢጫዎቹን መሪ ለማድረግ የተቃረበ አጋጣሚ ነበር። በአጋማሹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢይዙም ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ባልቻሉት ሲዳማ ቡናዎች በኩልም ፌድሪክ ኑሲ በመቀስ ምት ያደረጋት ሙከራ ትጠቀሳለች።

 

ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴና ፉክክር የተደረገበት እንዲሁም ሲዳማ ቡናዎች ከተጋጣሚያቸው የተሻለ ብልጫ የወሰዱበት ነበር። ዳዊት ገብሩ ከቀኝ መስመር ተጫዋች አታሎ አሻግሯት ከግቡ አፋፍ የነበረው እንዳልካቸው ጥበቡ ያልተጠቀመባት ቢጫዎቹን መሪ ለማድረግ የተቃረበች አጋጣሚ የአጋማሹ የመጀመሪያ ሙከራ ስትሆን ቀጥለው በነበሩ ደቂቃዎችም ሲዳማ ቡናዎች የተሻለ ጫና ፈጥረው ሙከራዎችም ያደረጉበት ነበር። መስፍን ታፈሰ ከእጅ ውርወራ የተሻገረችለትን ኳስ ተጠቅሞ በጥሩ መንገድ ተጫዋች ካታለለ በኋላ ያደረጋት ዒላማዋን ያልጠበቀች ሙከራ እንዲሁም ሬድዋን ናስር ከቆመ ኳስ በቀጥታ መቷት ግብ ጠባቂው ሙታክብዋ ጆኤል በእግሩ የመለሳት ኳስም ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎች ነበሩ። ከተጠቀሱት ሙከራዎች በተጨማሪ ኢያሱ ሮንዳ ከቆመ ኳስ አክርሮ መቷት ሙታክንዋ ጆኤል ከመለሳት በኋላ ከግቡ አፋፍ የነበረው ይሳቅ ካኖ በድጋሜ መቷት ግብ ጠባቂው በጥሩ ቅልጥፍና ያዳናት ወርቃማ አጋጣሚም ሲዳማ ቡናዎችን መሪ ለማድረግ የተቃረበች አጋጣሚ ነች።

ሁለቱም ቡድኖች በሁለቱም አጋማሾች እየተፈራረቁ ብልጫ የወሰዱበት ጨዋታም ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።