ኢትዮጵያ መድን በጨዋታ ሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን 3 ለ 0 አሸነፈ።
ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ የወሰዱበት እና ጥሩ ፉክክር የተደረገበት የመጀመሪያው አጋማሽ በሙከራዎች የታጀበ ነበር። በኢትዮጵያ መድን በኩል ብሩክ ሙልጌታ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተከላካይ ብሩክ ታረቀኝ ሳጥኑ አቅራቢያ የሰራውን ስህተት ተከትሎ ያገኛትን ኳስ በመጠቀም ያደረጋት ሙከራ ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረበች አጋጣሚ ስትሆን ቀጥሎም ፈረሰኞቹ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። ሀብታሙ ጉልላት ከቀኝ መስመር ፍፁም ጥላሁን ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ አክርሮ መቷት አቡበከር ኑራ ያዳናት እና ፀጋ ከድር የተመለሰችውን ኳስ በድጋሜ መቶ ግብ ጠባቂው በጥሩ ቅልጥፍና ያዳነበት አጋጣሚም ለፈረሰኞቹ አስቆጪ ሙከራዎች ነበሩ።

ከዚህ በተጨማሪ ብርሀኑ አሻሞ ከቅጣት ምት መቷት አቡበከር ኑራ ከመለሳት በኋላ ከግቡ አፋፍ የነበረው ሀብታሙ ጉልላት ወደ ግብነት ያልቀየራት ኳስም ፈረሰኞቹ ከፈጠሯቸው ዕድሎች ትጠቀሳለች። ከተጠቀሱት ሙከራዎች በኋላ መጠነኛ ብልጫ የወሰዱት መድኖች ረመዳን የሱፍ በግንባሩ እንዲሁም ዳዊት አውላቸው ካደረጓቸው ሙከራዎች በኋላም በ41ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ብሩክ ሙልጌታ ከአማካዩ ወገኔ ገዛኸኝ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ያስቆጠራት ግብም ቡድኑን መሪ ማድረግ ችላለች።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳይደረግበት ከቆየ በኋላ ፈረሰኞቹ አቻ የሚሆኑበትን ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር፤ ፍፁም ጥላሁን አሻምቶት ከግቡ አፋፍ የነበረው ተገኑ ተሾመ በግንባሩ ከገጨው በኋላ አቡበከር ኑራ በድንቅ ብቃት ያዳነው ሙከራም ቡድኑን ወደ ጨዋታው ለመመለስ የተቃረበ ነበር። በግብ ጠባቂው ጥረት ግብ ከመሆን ከተረፈው ኳስ በኋላም ኢትዮጵያ መድኖች መሪነታቸውን ያጠናከሩበት ግብ ማስቆጠር ችለዋል፤ ረመዳን የሱፍ ከተከላካይ ጀርባ የጣለውን ኳስ ተጠቅሞ ብሩክ ሙልጌታ በጥሩ ቅልጥፍና ደርሶ ከመረብ ጋር ያዋሀዳት ኳስም የቡድኑን መሪነት ከፍ ማድረግ ችላለች።

ፈረሰኞቹ ከግቡ መቆጠር በኋላ የተሻለ ጫና ፈጥረው ከመአዝን ተሻምቶ ብርሀኑ አሻሞ በግንባር ባደረገው ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ኢትዮጵያ መድን 88’ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በላቸው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተከላካይ አሚን ነስሩ የፈጠረውን ስህተት ተጠቅሞ ባስቆጠረው ግብ ጨዋታውን 3 ለ 0 ማሸነፍ ችለዋል።

