በ21ኛ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን የሚካሄዱ መርሐ ግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ !

አዳማ ከተማ ከ ሸገር ከተማ
በመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ 7 ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ ተቀዳጅቶ የነበረው አዳማ ከተማ ሁለተኛውን ዙር ግን በጥሩ መነሳሳት በድል ጀምሯል። ኢትዮጵያ መድንን በቢኒያም ዐይተን የፍጹም ቅጣት ምት ግብ ያሸነፈው ቡድኑ ሦስተኛው ክፍል ላይ በደካማ አደረጃጀት እያባከናቸው የሚገኙ አጋጣሚዎችን በተሻለ ደረጃ መጠቀም የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ዋነኛ ሥራ ይሆናል።
ከመጨረሻ 12 ጨዋታዎች በአንድ ጨዋታ (ከመቻል ጋር በተደረገ) ብቻ ድል ማድረግ የቻለው ሸገር ከተማ የሁለተኛ ዙር የመክፈቻ ጨዋታውንም ያለ ግብ አጠናቋል። አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ከኃላፊነታቸው በማንሳት ከተለያዩ አሰልጣኞች ጋር ሲነጋገር የነበረው ቡድኑ በስተመጨረሻም ረዳት አሰልጣኝ የነበሩትን ዶክተር ኢያሱ መርሐጽድቅ ወደ ዋና አሰልጣኝነት በማምጣት ያደረገውን የመጀመሪያ ጨዋታ ያለ ግብ የቋጨ ሲሆን ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ብቻ ርቆ የተቀመጠውን ቡድን ወደ ውጤት መመለስ ደግሞ የአዲሱ አሰልጣኝ የመጀመሪያ ፈተና ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ
ተከታታይ ሁለት የ1ለ1 የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ብርቱካናማዎቹ በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ብርቱ ፉክክር አድርገው ከዕረፍት መልስ በተቆጠረባቸው ግብ ነጥብ ቢጋሩም የነበራቸው ተነሳሽነት ግን የአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለን ልብ የሚያሞቅ ነበር። ሆኖም ቡድኑ ካለበት የሰንጠረዡ ወገብ ከፍ ብሎ ተደላድሎ ለመቀመጥ የዛሬውን ድል አብዝቶ ይፈልገዋል።
በመቻል 2ለ0 ከመመራት ተነስተው 4ለ3 ያሸነፉት የጦና ንቦቹ በዚህ የውድድር ዓመት ምርጡን ብቃታቸውን ባሳዩበት ጨዋታ በተለይም ከዕረፍት መልስ የነበራቸው ብልጫ እጅግ ማራኪ ነበር። ለአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ራስ ምታት የሆነው የመከላከል አደረጃጀቱ ዝንጉ መሆን የሚታረም ከሆነ ቡድኑ ከወራጅ ቀጠናው አካባቢ ካሉ ቡድኖች በሚያሳየው እንቅስቃሴ ካለበት ደረጃ ከፍ ለማለት ከሌሎቹ የተሻለ አቅም እንዳለው በተደጋጋሚ ዐሳይቷል።
ድሬዳዋ ከተማ ያሬድ ታደሰ ፣ ሬድዋን ሸረፋ ፣ አድናን መኪ እና አያልኔ እንድሪስን በጉዳት ምክንያት አያገኝም። በወላይቻ በኩል ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ አስራ ዘጠኝ ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ስድስቱ ጨዋታዎች በነጥብ መጋራት ሲደመደሙ ድሬዳዋ ከተማዎች በዘጠኝ እንዲሁም ወላይታ ድቻዎች ደግሞ በአራቱ ባለድል መሆን ችለዋል በጨዋታዎቹ ድሬዎች 21 እንዲሁም ድቻዎች ደግሞ 15 ግቦችን አስቆጥረዋል።
መቻል ከ መቐለ 70 እንደርታ
ካለው የስብስብ ጥራት አንጻር ደካማ አፈጻጸም እያሳየ የቀጠለው መቻል በተደጋጋሚ እንደ ቀላል በሚጥላቸው ነጥቦች ኮስታራነትን ከሚፈልገው ከመሪነቱ ፉክክር ወደኋላ እያለ ይገኛል። ቡድኑ ተከታታይ 3 ድሎችን ካሳካ በኋላ ባደረጋቸው የመጨረሻ 3 ጨዋታዎች በሁለቱ ሲሸነፍ በአንዱ ነጥብ ተጋርቷል። የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት አቀራረብ ጠንካራ ቢመስልም በተለይም መምራት ሲጀምሩ ቡድኑ ላይ የሚታየው “ጨዋታውን ተቆጣጥረነዋል ፤ አልቋል” ዐይነት የዝንጉነት ስሜት ሊታረም የሚገባው ነው።
ሽረ ምድረገነትን አሸንፎ ሁለተኛውን ዙር የጀመረው መቐለ 70 እንደርታ ከወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ ተቀምጦ የሚያደርገውን ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ለቀጣይ ጉዞው የሚፈጥርለት መነሳሳት ትልቅ ነው። ቡድኑ የሚያስቆጥረው ግብ ከመቀነሱ ውጪ ባለፉት 10 ጨዋታዎች አንዱን ብቻ መሸነፉ በበስነልቦና ረገድ ጠንካራ ሆኖ እንዲዘልቅ እያስቻለው ነው። አሰልጣኝ ጸጋየ ኪዳነማርያም ቡድኑን ከያዙት በኋላ በተለይም በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻሻለውን ቡድናቸውን በድል አጅበው ለመቀጠል ከፍተኛ የስብስብ ጥራት ላለው መቻል የሚሆን ምን ዓይነት አቀራረብ ይይዛሉ የሚለው የሚጠበቅ ነው።
መቻል ውብሸት ጭላሎ እና ዮሐንስ መንግሥቱን ሙሉ ለሙሉ በጉዳት ሲያጣ የአማኑኤል ዮሐንስ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው። የመቐለን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
ሁለቱ ክለቦች 7 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ እኩል ሦስት ሦስት ተሸናንፈው አንዱ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ጨዋታ ነው። በግንኙነቱ መቐለ 9 ሲያስቆጥር ጦሩም 9 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል ( የመጀመሪያው ዙር በፎርፌ በመቻል 3ለ0 አሸናፊነት በመመዝገቡ የግብ ብዛት ቁጥሮቹ አብረው የተደመሩ ናቸው)።
ነጌሌ አርሲ ከ ኢትዮጵያ ቡና
ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ነጥብ የተጋሩት ነጌሌዎች በዚህ ጨዋታ ላይ ከ30 በላይ ደቂቃዎች በቀይ ካርድ ምክንያት የቁጥር ብልጫ ቢያገኙም ሊጉን በነጥብ በልጠው ሊመሩ የሚችሉበትን ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። አሰልጣኝ ቱሉ ደስታ በመጀመሪያው ዙር ከዛሬው ተጋጣሚያቸው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረጉት ጨዋታ 2ለ1 የተረቱበትን አጋጣሚ አስታውሰው ቡድናቸውን ወደ ድል ለመመለስ ጠንካራ ተጋጣሚ ሆነው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል።
ሸገር ደርቢ በመራዘሙ ምክንያት በሁለተኛው ዙር ጨዋታ ያላደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓላቸውን ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከሚመራው የደቡብ ሱዳኑ JAMUS ክለብ ጋር ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ 2ለ0 የተሸነፉ ሲሆን ከዕለት ዕለት እየቀነሰ የመጣውን የተጫዋቾችን የጨዋታ ፍላጎት ማነስ ማስተካከል በቅርቡ ቡድኑን ለተረከቡት አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ለነገ የማይባል ሥራ ነው።

