ሪፖርት | ነብሮቹ እና አዞዎቹ ወሳኝ ድል ተጎናፀፉ

ሪፖርት | ነብሮቹ እና አዞዎቹ ወሳኝ ድል ተጎናፀፉ

በሀዋሳ በተካሄዱ ጨዋታዎች ሀድያ ሆሳዕና ኢትዮ ኤሌክትሪክን አንድ ለባዶ ሲያሸንፍ አርባምንጭ ከተማ ባህርዳር ከተማን ሁለት ለባዶ ረቷል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ሀድያ ሆሳዕና

9፡00 ሰዓት የተጀመረው የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ በተደረገበት አጋማሽ በሀድያ ሆሳዕና በኩል እዮብ አለማየሁ በፈጣን ሽግግር የተገኘችውን ኳስ ታግሎ ለብሩክ በየነ ካቀበለው በኋላ ተጫዋቹ ከሳጥኑ የግራ ክፍል መቷት ግብ ጠባቂው የመለሳት ኳስ ተጠቃሽ ናት።
የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ በነበራቸው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በኩልም አቤል ሀብታሙ በጥሩ መንገድ ሰንጥቋት አንዋር በድሩ ከመታት በኋላ
ግብ ጠባቂው ያዳናት እንዲሁም ያሬድ የማነ ከቆመ ኳስ አሻምቷት በረከት ወ/ዮሐንስ በግንባሩ ያደረጋት ሙከራ ይጠቀሳሉ።

ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ፉክክር የተደረገበት ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ በርከት ያሉ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎችም በሀድያ ሆሳዕና በኩል  እዮብ አለማየሁ በረዥሙ ተሻግራ ብሩክ በየነ በግንባሩ የገጫትን ኳስ ተጠቅሞ ከመምታቱ በፊት የሱፍ ሞሮ ወጥቶ ያዳናት አጋጣሚ እንዱሁም በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ደግሞ አሸናፊ ጥሩነህ ከሳጥኑ የግራ ክፍል አክርሮ መቷት በግቡ አፋፍ የነበረው ሀሰን ሑሴን በስህተት የመለሳት ኳስ እና አሸናፊ ጥሩነህ ከርቀት አክርሮ መቷት ለጥቂት ከፍ ብላ የወጣችው ሙከራ ተጠቃሽ የግብ አጋጣሚዎች ናቸው።

በ79ኛው ደቂቃ ደግሞ ጫላ ተሺታ በፈጣን ሽግግር ሂደት ያገኛትን ኳስ በጥሩ መንገድ ከሰነጠቃት በኋላ ተቀይሮ የገባው ደስታ ዋሚሾ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ ነብሮቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር ጥቂት ደቂቃዎች በኋላም ጫላ ተሺታ በተመሳሳይ ሂደት ያገኛትን ኳስ ከግቡ አፋፍ ነፃ ለነበረው እዮብ አለማዮህ አቀብሎት አጥቂው ወደ ግብነት ያልቀየራት አጋጣሚም ለነብሮቹ አስቆጪ አጋጣሚ ነበረች።

በተሻለ መንገድ ለማጥቃት ጥረት ባደረጉበት ክፍለ ጊዜ ግብ ለማስተናገድ የተገደዱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮችም ፓትሪክ ሲቦማና ከመዓዝን ተሻግራ በግንባሩ ሞክሯት ግብ ጠባቂው ባዳናት እና ከርቀት አክርሮ መቷት በድጋሜ በግብ ጠባቂው ድንቅ ብቃት በተመለሰች ሁለት ሙከራዎች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ጨዋታው በሀድያ ሆሳዕና 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ባህርዳር ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ

የጣና ሞገዶቹ እና አዞዎቹ ያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ መርሐ ግብር በመጀመሪያው አጋማሽ ባህርዳር ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱበት ቢሆንም በማጥቃቱ ረገድ ግን አርባምንጭ ከተማዎች የተሻለ የተንቀሳቀሱበት ነበር።

አዞዎቹ በጅማሮው ጄሮም ፍሊፕ ከመሀል ሜዳ አከባቢ በጥሩ መንገድ ኳስ እየገፋ ወደ ሳጥን ገብቶ በግሩም መንገድ አጥፎ ሞክሮት ግብ ጠባቂው በመለሰበት እጅግ ለግብ ሙከራ ካደረጉ በኋላም 19ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ታምራት ከግራ መስመር አሻምቶት ቡታቃ ሸመና በግንባሩ ባስቆጠረው ግብ መሪ መሆን ችለዋል። ከግቡ መቆጠር ከደቂቃዎች በኋላም ባህርዳር ከተማዎች መሳይ አገኘሁ አሻግሮት አንተነህ ተፈራ በግምባሩ ባደረገው ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም በ31ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል፤ ጄሮም ፍሊፕ በራሱ ጥረት አግኝቶ ሰንጥቋት ይድነቃቸው ያሲን በጥሩ መንገድ አፈትልኮ ከመረብ ጋር ያዋሀዳት ኳስም የአዞዎቹን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችላለች።

በአጋማሹ መገባደጃ ላይ ዮሐንስ መንግስቱ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል አክርሮ መቶት ግብ ጠባቂው በጥሩ ሁኔታ የመለሰው ኳስም ባህርዳር ከተማዎችን ወደ ጨዋታው ለመመለስ የተቃረበ አጋጣሚ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋቾች ለውጥ አድርገው የተመለሱት ባህርዳር ከተማዎች ብልጫ የወሰዱበት ሲሆን በዚህም አንተነህ ተፈራ ተቀይሮ የገባው ሰቲህ ኦሴ በጥሩ መንገድ ገፍቶ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ መቶት አካሉ አቲሞ ተደርቦ ባወጣው እና አንተነህ ተፈራ ከቀኝ መስመር አሻግሮት አማኑኤል ገ/ሚካኤል በግንባር ባደረገው ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል።

በአጋማሹ መሪነታቸውን ለማስጠበቅ አፈግፍገው በተጫወቱት አርባምንጭ ከተማዎችም በፍቅር ግዛቸው ከርቀት አክርሮ መቶት ግብ ጠባቂው ወደ ውጭ ባወጣው ያልተጠበቀ ሙከራ ግብ ለመግኘት ተቃርበው ነበር። የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መያዝ ቢችሉም በቂ የግብ ዕድሎች መፍጠር ያልቻሉት የጣና ሞገዶቹ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በማንያዘዋል ካሳ እና ብሩክ ሰሙ አማካኝነት ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በአርባምንጭ ከተማ 2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።