ምድረ ገነት ሽረ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እንዲሁም ወልዋሎ ዓ/ዩ ፋሲል ከነማን 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

ምድረ ገነት ሽረ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከድል እና ከሽንፈት ማግስት የተመለሱ ቡድኖችን ባገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ምድረ ገነት ሽረዎች በኳስ ቁጥጥር እና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ረገድ ብልጫ ነበራቸው። ነገር ግን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ደርሰው ይህ ነው የሚባል ጥራት ያለው የግብ አደጋዎችን መፍጠር ሳይችሉ የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ልክ እንደተጀመረ በ48ኛው ደቂቃ ምድረ ገነት ሽረዎች በፈጣን መልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ዳንኤል ዳርጌ ከሶስት ተጫዋቾች ጋር ታግሎ ከሳጥን ውጪ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ ወደ ግብነት ተቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ያለ ግብ ሙከራ ያስመለከተን ጨዋታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ተቀይሮ የገባው ናትናኤል ዳንኤል 90ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ የቻለ ሲሆን ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ 90+3 ላይ ከሜዳው የቀኝ መስመር ከአዲሱ መገርሳ የተቀበለው ኳስ አስቆጥሮ ግብነት ተቀይሮ ባለቀ ደቂቃ ቡድኑን አቻ አድርጓል።

የመጨረሻ ደቂቃ ድራማዊ ክስተቶችን ባስመለከተን ጨዋታ የዳኛው ፊሽካ የጨዋታውን መጠናቀቅ ለማብሰር በሚጠበቅበት ሰዓት ከማዕዘን ምት የተሻገረውን እና በብዙ ተጫዋቾች ተገጫጭቶ የደረሰውን ኳስ ተቀይሮ የገባው የክለቡ አዲሱ ፈራሚ ደሳለኝ ከተማ በግንባሩ በመግጨት ግብ አስቆጥሮ የማታ ማታ ለደቂቃዎች የተነጠቁትን ደስታ አስመልሷል። ጨዋታውም በምድረ ገነት ሽረ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ፋሲል ከነማ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ
ፋሲል ከነማን ከ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ባገናኘው የምሽቱ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ፈጣን በሆነ ሽግግር በሜዳው ሶስተኛ ክፍል ላይ መድረስ ችለዋል። በፋሲል ከነማ በኩል 30ኛው ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም ሞክሮ በግብ አግዳሚ በወጣበት ሙከራ ለግብ መቅረብ ችለዋል። ይህ ሙከራ ከተደረገ ከ10 ደቂቃዎች በኋላ 40ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት ተሻግሮ ብሩክ እንዳለ በአግባቡ ያላራቀውን ኳስ ዣቪዬር ሙሉ በግራ እግሩ መቶ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ በ49ኛው ደቂቃ ፋሲል ከነማዎች በቃልኪዳን ዘላለም አማካኝነት ሙከራ ማድረግ ሲችሉ 60ኛው ደቂቃ ወልዋሎ አዲግራቶች አቻ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። የሜዳው የግራ የሳጥን ክፍል ላይ ዳዊት ገብሩ ያቀበለውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሞይስ ፓውቲ መቆጣጠር ባለመቻሉ ያገኘውን ዕድል ተቀይሮ የገባው ኤፍሬም ሃይለማርያም ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ በተሰጡት ጭማሪ ደቂቃዎች ወልዋሎ አዲግራቶች በመልሶ ማጥቃት ያገኙት እና ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ ኮንኮኒ ሃፊዝ የተከላካዮችን መዘናጋት ተከትሎ ኳስንና መረብን በማገናኘት ቡድኑን ከመመራት ተነስቶ አሸናፊ መሆን የቻለበትን ግብ አስቆጥሯል። ውጤቱንም ተከትሎ ፋሲል ከነማዎች ሶስተኛ ተከታታይ ሽንፈታቸውን በማስተናገድ ወደ ዋንጫ የሚያስወጣቸውን ገመድ በገዛ መቀሳቸው መቁረጥ ጀምረዋል።

