ሲዳማ ቡናዎች በአቤል ያለው ግብ እንዲሁም ፋሲል ከነማዎች በታምራት ኢያሱ ግብ ተጋጣሚዎቻቸውን ማሸነፍ ችለዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሲዳማ ቡና
ሁለቱ ቡድኖችን ባገናኘው የጋራው ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች በቁጥር በዛ ብለው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉ ሲሆን 36ኛው ደቂቃ ላይ በፍራኦል መንግስቱ የቆመ ኳስ የግብ ሙከራ ማድረግ ችለዋል።የአጋማሹ መደበኛ የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ በተሰጡት ጭማሪ ደቂቃ ከቆመ ኳስ የተሻገረውን እና በደስታ ደሞ የተጨረፈውን ኳስ ያገኘው አቤል ያለው ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ አድርጎ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመሩ አድርጓል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ራሳቸውን አሻሽለው ወደ ሜዳ የተመለሱት ንግድ ባንኮች የአቻነት ግብ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ በነበረበት ሰዓት 55ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂያቸው ጊቢ ጆቤ ኳስ ከሳጥን ውጭ በእጅ መንካቱን ተከትሎ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

ይህም ቀሪውን ደቂቃ ከባድ እንዲሆንባቸው ያደረገ ቢሆንም ነገር ግን ንግድ ባንኮች የቁጥር ብልጫው ሳይበግራቸው ወደፊት በመጠጋት የአቻነት ግብ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረቶችን ቢያደርጉም ጠንካራውን የሲዳማ ቡና የግብ አጥር መናድ ተስኗቸው ጨዋታው አቤል ያለው ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ 1-0 ተጠናቋል።
ወላይታ ድቻ ከ ፋሲል ከነማ
ወላይታ ድቻና ፋሲል ከነማን ባገናኘው ጨዋታ ቀዝቃዛ ያለ ጅማሮ የነበሩው ቢሆንም 20ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል ከነማዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ ታምራት ኢያሱ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ዐፄዎቹን መሪ አድርጓል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ወላይታ ድቻዎች በፈጣን የመስመር አጥቂዎች ዒላማ ያደረገ ሙከራዎችን መሰንዘር የቻሉ ሲሆን ፋሲል ከነማዎች ወደ ኋላ በቁጥር በዛ ብለው በማፈግፈግ ጥንቃቄ የተሞላበትን አጫወት መጫወት ምርጫቸው በማድረግ የመጀመሪያውን አጋማሽ ግብ ሳይቆጠርባቸው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከእረፍት መልስ ራሳቸውን በሚገባ አጠናክረው የአቻነት ግብ ለማግኘት ጥረታቸውን የቀጠሉት ወላይታ ድቻዎች 54ኛው ደቂቃ ላይ በቅብብል ካርሎስ ዳምጠው ከቆመ ኳስ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም በግብ ጠባቂው ጥረት ተጨርፎ ወጥቶባቸዋል። በድጋሚ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ውብሸት ክፍሌ በግንባሩ ገጭቶ ቢሞክረውም ግብ ሳይሆን ቀርቷል።

ከዚህ በተጨማሪ ወላይታ ድቻዎች በካርሎስ ዳምጠውና በያሬድ ዳርዛ የግብ ድሎችን መፍጠር የቻሉ ቢሆንም ተጨማሪ ግብ ሳንመለከት ጨዋታው በፋሲል ከነማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።”

