ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዳግም ወደ ድል ሲመለስ ነብሮቹና ቡናማዎቹ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዳግም ወደ ድል ሲመለስ ነብሮቹና ቡናማዎቹ ነጥብ ተጋርተዋል

በአበበ ቢቂላ ስታድየም በተካሄዱ የ27ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ አዳማ ከተማን 1 ለ 0 ሲረታ ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት የሀድያ ሆሳዕና እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ 2 ለ 2 ተጠናቋል።

አዳማ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በተለያየ ወቅታዊ አቋም የሚገኙ ቡድኖች ያገናኘው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረገበት እና ኤሌክትሪኮች የተሻለ ብልጫ የወሰዱበት ነበር።
በአጋማሹ ወደ ግብ የቀረበ ሙከራ ባያደርጉም ከተጋጣሚያቸው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር በመያዝ ዕድሎች የፈጠሩት ኤሌክትሪኮች 43ኛው ደቂቃ ላይ
መሪ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል። ያሬድ የማነ እና በዛብህ መለዮ በቀኝ መስመር በኩል በጥሩ መንገድ ከተቀባበሉ በኋላ ያሬድ የማነ ወደ ግብነት የቀየረው ኳስም ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ኤሌክትሪኮች ከግቡ መቆጠር በኋላም አሸናፊ ጥሩነህ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቶት ግብ ጠባቂው በመለሰው ኳስ እና ሐሰን ሁሴን የተመለሰውን ኳስ ከመምታቱ በፊት ተከላካዮች ተረባርበው ባወጡት አጋጣሚ መሪነታቸው ለማስፋት ተቃርበው ነበር።

ጥሩ ፉክክር እና በርካታ የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበት ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች የተደረገበት ነበር።
አቡበከር ሳኒ እና ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ በግምባር ያደረገው ሙከራ በአዳማ ከተማ በኩል በረከት ወልደ ዮሐንስ ከግራ መስመር የተሻማችውን ኳስ በግምባሩ ገጭቷት ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችው ድንቅ ሙከራም በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል የተደረጉ የአጋማሹ ቀዳሚ ሙከራዎች ናቸው።

ከተጠቀሱ አጋጣሚዎች በኋላ አቤል ሀብታሙ በድንቅ ሁኔታ ከመሀል ሜዳ ወደ ሳጥን ገፍቶ በመግባት መቷት አግዳሚው የመለሳት ኳስ የኤሌክትሪክን መሪነት ከፍ ለማድረግ የተቃረበች ሙከራ ስትሆን ከደቂቃዎች በኋላም ሳሙኤል ዮሐንስ አሻምቷት ግብ ጠባቂው ከመለሳት በኋላ ማይክል ኪፕሩቪ ወደ ግብ መቷት እስማኢል ናሂማና ከግቡ መስመር የመለሳት ወርቃማ አጋጣሚ አዳማ ከተማን አቻ ለማድረግ ተቃርባ ነበር።

እዮብ ገብረማሪያም በጨዋታው መገባደጃ ላይ አብነት ተስፋዬ በግሩም የመልሶ ማጥቃት ሂደት አግኝቶ ያመቻቸለትን ኳስ በመምታት ያልተጠቀመባት አጋጣሚም የጨዋታው የመጨረሻ የግብ ሙከራ ስትሆን ጨዋታውም በኢትዮ ኤሌክትሪክ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀድያ ሆሳዕና ከ ኢትዮጵያ ቡና

በደማቅ የደጋፊዎች ህብረ ዝማሬ እና በሁሉም የሜዳ ክፍሎች በነበሩ አካላዊ ፍልሚያዎች ታጅቦ የተካሄደው የነብሮቹ እና የቡናማዎቹ ጨዋታ  ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት ነበር።

አጋማሹ አቡበከር አዳሙ ከቅጣት ምት በቀጥታ ካደረጋት ዒላማዋን የጠበቀች ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል የግብ አጋጣሚ ሳያስተናግድ ከዘለቀ በኋላም በ28ኛው ደቂቃ ላይ በማጥቃቱ ረገድ የተሻለ ብልጫ የነበራቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች መሪ የሆኑበት ግብ አስቆጥረዋል።  በረዥሙ ተሻግራ የሀድያ ሆሳዕና ተጫዋቾች ከመለሷት በኋላ አቡበከር አዳሙ አመቻችቷት ዘላለም አባተ የተከላካዮችን አለመናበብ ተጠቅሞ መረቡ ላይ ያሳረፋት ግብም ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ነች።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ቃልአብ ውብሸት ከመዓዝን ተሻምታ በነፃ አቋቋም ሆኖ በግምባር ባደረጋት ሙከራ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ የፈጠሩት ነብሮቹም 40ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ አለማዮህ ከቀኝ መስመር የተሻማችውን ኳስ ተጠቅሞ በግምባሩ ባስቆጠራት ግብ አቻ መሆን ችለዋል። ሆኖም ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ቡናማዎቹ ፉዐድ ኢብራሂም ከቆመ ኳስ አሻምቷት ራምኬል ጄምስ በግምባሩ ባስቆጠራት ግብ ዳግም ወደ መሪነት በመመለስ አጋማሹን ማጠናቀቅ ችለዋል።

ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ እንደ መጀመርያው አጋማሽ ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት ሲሆን ጅማሮው ላይ ተመስገን ብርሀኑ በመልሶ ማጥቃት ከደስታ ዋሚሾ የተቀበላትን ኳስ በጥሩ መንገድ ወደ ሳጥን ገፍቶ በመግባት መቷት ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችው ሙከራም ነብሮቹን ዳግም ወደ አቻነት ለመመለስ የተቃረበች ቀዳሚ ሙከራ ነች።

አጋማሹ በጥሩ ፉክክር ቀጥሎ ዘላለም አባተ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቷት ግብ ጠባቂው ከመለሳት በኋላ አማኑኤል አድማሱ የተመለሰችውን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት እና ኦውሱ እንድሪው ያዳናት ወርቃማ አጋጣሚ የቡናማዎቹ መሪነት ከፍ ለማድረግ የተቃረበች ሙከራ ስትሆን ሀድያዎችም
ፀጋአብ ግዛው ከረዥም ርቀት ከቆመ ኳስ በቀጥታ መቷት የግቡ አግዳሚ በመለሳት ድንቅ ሙከራ የአቻነት ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር።

ብርቱ ፉክክር በተደረገበት የጨዋታው መገባደጃ ላይም ሀድያ ሆሳዕናዎች በ88ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ብሩክ በየነ በጥሩ ቅብብል ተጋጣሚ ግብ ክልል ደርሳ ጫላ ተሺታ ከሳጥኑ ቀኝ ክፍል ያሻገራትን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም ነብሮቹን አቻ ያደረገች ግብ ነች።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩትም አማኑኤል አድማሱ ከቀኝ መስመር ተሻምታ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ከፍ አድርጎ መቷት ግብ ጠባቂው ኦውሱ እንድሪው ባድናት እንዲሁም  በድጋሜ አማኑኤል አድማሱ የተመለሰችውን ኳስ አመቻችቶለት አቡበከር አዳሙ ከግቡ ቅርብ ርቀት ሆኖ መቷት ግብ ጠባቂው ኦውሱ እንድሪው  በድንቅ ብቃት ያወጣት ሙከራ ቡናማዎቹን ባለ ድል ለማድረግ የተቃረቡ ሁለት ወርቃማ አጋጣሚዎች ነበሩ።  በሁለቱም አጋማሾች ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታም በአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።