ሸገር ከተማዎች ከሶስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ሲመልሱ ሁለት ቀይ ካርድ በታየበት ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ መድን ነጥብ ተጋርተዋል

ባህር ዳር ከተማ ከ ሸገር ከተማ
የመጀመሪያውን ግብ ለመመልከት 23 ደቂቃዎችን በፈጀው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሸገር ከተማዎች መሪ መሆን የቻሉበትን አስደናቂ ግብ አስቆጥረዋል። ቢንያም ፍቅሩ የግብ ጠባቂውን ከግብ መውጣት ተመልክቶ ከገዛ የሜዳ ክልሉ አክርሮ የመታው ኳስ ግሩም በሆነ አጨራረስ መረብ ጋር ተገናኝቶ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። በድጋሚ በ31ኛው ደቂቃም በመልሶ ማጥቃት ከግብ ጠባቂ የተሻገረን ኳስ አሚር አብዱ ካሻማው በኋላ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ቡልቻ ሹራ በግንባሩ በመግጨት የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት አሳድጓል።

ከግቦቹ መቆጠር በኋላ ባህር ዳር ከተማዎች ኳስን በጥሩ ሁኔታ በመቀባበል ወደ ተቃራኒ ግብ ክልል መድረስ የቻሉ ቢሆንም በመሳይ አገኘው እና በብሩክ ሰሙ አማካኝነት የተሞከሩት ኳሶች በግብ ሸገር መሪነቱን ይዞ እንዲቀጥል ትልቅ ድርሻ በተወጣው ግብ ጠባቂው ባህሩ ነጋሽ ንቃትና ጥረት ሳይሳኩ ቀርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይረው በማስገባት የተሻለ ጫና መፍጠር የቻሉት ባህር ዳር ከተማዎች በአንተነህ ተፈራ እና ሰቲህ ኦሴ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ቢያደርጉም የሸገርን ጠንካራ የመከላከል አጥር ግን መስበር አልቻሉም በዚህም ጨዋታው በሸገር ከተማ 2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ መድን
በኳስ ቁጥጥር ረገድ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በብሩክ በላቸው አማካኝነት የግብ አግዳሚውን የገጨ ሙከራ ሲያደርጉ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው በበዛብህ መለዮ እና በሀሰን ሁሴን በኩል የሰነዘሯቸው ጥቃቶች ደግሞ በግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ጥረት ሳይሳኩ ቀርተዋል። ምንም እንኳን ጥረቶች ቢደረጉም፣ የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ግብ በዜሮ ለዜሮ ውጤት ተጠናቋል።

በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ዋና ዳኛ መስፍን ዳኜ በሁለቱም ወገን የቀይ ካርድ ውሳኔዎችን አስተላልፈዋል። በ59ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪኩ ሀሰን ሁሴን በመድን ተጫዋች ላይ በፈጸመው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሲሰናበት በ65ኛው ደቂቃ ደግሞ የኢትዮጵያ መድኑ አብዱልጋኒዩ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። በዚህም ሁለቱም ቡድኖች ቀሪውን ጊዜ በአሥር ተጫዋቾች ለመቀጠል ተገደዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ጥፋት ከተሰራበት ቦታ ያገኙትን የቅጣት ምት በዛብህ መለዮ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ግሩም በሆነ መንገድ አስቆጥሮ ኢትዮ ኤሌክትሪኮችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ አምስት ያክል ደቂቃዎች ሲቀሩት ከቅጣት ምት ግሩም ሙከራ ማድረግ የቻለው አማኑኤል ኤርቦ ያሬድ ካሳሁን ያሻማውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ ሆኖበግንባሩ በመግጨት ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን በጨዋታው ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ አድርጓል።

