ተጠባቂ በነበረው እና ብርቱ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ የዓምናው የፍጻሜ ተፋላሚ ሲዳማ ቡና ነገሌ አርሲን በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜ የተቀላቀለ አራተኛ ቡድን ሆኗል

በሁለቱም ቡድኖች በኩል በነበሩ በርካታ ተጓዥ ደጋፊዎች ዝማሬ ታጅቦ በተጀመረው ተጠባቂ ጨዋታ ቡድኖቹ በፈጣን ሽግግሮች የታጀበ የጨዋታ እንቅስቃሴ ያስመለከቱን ሲሆን 23ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች ተሳክቶላቸው ሮኅቦት ሰላሎ በአግባቡ ያላራቀውን ኳስ አቤል ያለው ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ነገሌ አርሲዎች በተጫዋች ቅያሪ ታግዘው ከፍተኛ ጫና መፍጠር ሲችሉ በተለይም ኪቲካ ጅማ በሁለት አጋጣሚዎች የግብ ሙከራዎች በማድረግ ተጋጣሚያቸው ላይ ጫና መፍጠር ችለዋል። የመጀመሪያው ሙከራው የግቡን አግዳሚ ታኮ ለጥቂት ወደ ውጭ ሲወጣ ሁለተኛው ደግሞ የግቡን ቋሚ ገጭቶ ተመልሷል።
ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከፍተኛ ጫና ሲፈጥሩ የነበሩት ነገሌ አርሲዎች በ59ኛው ደቂቃ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቷል፤ ተቀይሮ የገባው ኪቲካ ጅማ የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ አላዛር ማርኔ የሰራውን ስህተት በአግባቡ ተጠቅሞ ኳሷን ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን አቻ አድርጓል።

ከግቡ መቆጠር በኋላም ብርቱ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች 76ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም መሪነታቸውን የጨበጡበትን ድንቅ ግብ አስቆጥረዋል። ዮሴፍ ዮሐንስ ሳይታሰብ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ የግቡ ማዕዘን ላይ በማሳረፍ አስደናቂ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ መሪነት መልሷል። ይህንንም ተከትሎ ተጠባቂ በነበረውና ብርቱ ፉክክር በታየበት ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።


