ሪፖርት| ባህር ዳር ከተማ እና ሽረ ምድረ ገነት ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት| ባህር ዳር ከተማ እና ሽረ ምድረ ገነት ነጥብ ተጋርተዋል

የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ29ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ 1 ለ 1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል

ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ በጀመረው ጨዋታ ላይ ባህር ዳር ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ቢችሉም ግብ በማስቆጠሩ ረገድ ቀዳሚ የነበሩት ግን ሽረ ምድረ ገነቶች ነበሩ። በ21ኛው ደቂቃ ተካልኝ ደጀኔ ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ የላከው ኳስ የግብ ጠባቂው ይገርማል መኳንንት ስህተት ታክሎበት መረብ ላይ በማረፉ ሽረን መሪ አድርጓል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ በቁጥር በዝተው ማጥቃት የጀመሩት የጣና ሞገዶቹ በ37ኛው ደቂቃ ላይ አንተነህ ተፈራ ተከላካዮችን በድንቅ ሁኔታ አልፎ የመታው ኳስ በግቡ ቋሚ ተመልሶ ሰለሞን ገብረክርስቶስን በመግጨት ወደ ግብነት ተቀይሮ የጣና ሞገዶቹን አቻ ማድረግ ችሏል። ከአፍታ ቆይታ በኋላም አንተነህ ተፈራ ግብ ጠባቂውን አልፎ የመታውን ኳስ አንተነህ ተስፋዬ ከመስመር ላይ በመለሰበት እንዲሁም ሄኖክ ይበልጣል እና አማኑኤል ገብረሚካኤል በሞከሩት ተከታታይ ሙከራዎች ባህር ዳር ከተማዎች ለሁለተኛ ግብ እጅግ ተቃርበው ነበር።

ከዕረፍት መልስ ሽረ ምድረ ገነቶች የተሻለ መነቃቃት አሳይተው ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት ጫና ለመፍጠር ቢጥሩም በመጨረሻው የማጥቃት መስመር ላይ የነበራቸው የውሳኔ ጥራት ማነስ ሙከራዎች ማድረግ አልቻሉም። በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የሚጠቀስ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳይደረግበትም ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች አንድ ለአንድ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።