ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ፈረሰኞቹን 2ለ0 በመርታት ደረጃቸው ሲያሻሽሉ አዞዎቹ ምዓም አናብስትን በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሰዋል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ የሁለተኛ ቀን ቀዳሚ ጨዋታ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ነበር ጅማሮውን ያደረገው። ቡድኖቹ ከኳስ ጋር በመቆየት ረገድ ደካማ የሚባል እንቅሰቃሴ ባያደርጉም ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ግን አልቻሉም።
በአጋማሹ ሁለቱም ቡድኖች ከቆመ ኳስ ቀዳሚ ለመሆን ጥረት ቢያደርጉም ፈረሰኞቹ ዕድሎችን በመፍጠር አኳያ ብልጫ ሲወስዱ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው የተመለሱት ንግድ ባንኮች በቆሙ ኳሶች አከታትለው ግቦችን አግኝተዋል። 54ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ብቻውን ሆኖ ያገኘው ናትናኤል ዳንኤል በግሩም አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ሲችል በድጋሚ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ያደረገችውን ግብ ልክ እንደ መጀመሪያው ግብ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር በእፎይታ ቀሪውን ደቂቃ እንዲጨርሱ አድርጓቸዋል።
ፈረሰኞቹ ከግቦች በኋላ በጋራ ወደ ሳጥን እየገቡ ወደ ጨዋታ የሚመለሳቸውን ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ግቦችን አስቆጥረው ትኩረታቸውን ሙሉ በሙሉ መከላከሉ ላይ ያደረጉትን የንግድ ባንኮች የተከላካይ መስመር ሰብረው ገብተው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሶስት ነጥብ በማስገኘት እና ደረጃቸውን ከፍ እንዲያደርጉ በማድረግ ተቋጭቷል።
መቐለ 70 እንደርታ ከ አርባምንጭ ከተማ
ገና በማለዳው የምዓም አናብስቶችን ተከላካይ መስመር በመፈተን የጀመሩት አዞዎቹ የመጀመሪያ ደቂቃ ላይ ጂሮም ፈሊፕ ግብ ጠባቂው መውጣቱን አይቶ ከፍ አድርጎ የመታው ኳስ ፍሬዘር ካሳ እንዴትም የመለሰበት ሙከራ መሪ ሊያደርጋቸው የቀረበ ሲሆን 5ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብልል የተገኘውን ኳስ ቡጣቃ ሸመና ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ አክርሮ በመምታት ሌላ ግብ ለመሆን የቀረበ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው በግሩም ሁኔታ አግዶበታል። ጨዋታው 14ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ አዛዎቹ በተደጋጋሚ ያደረጉት ጥረት ፍሬ አፍርቶ ግብ አስቆጥረዋል፤ ይገዙ ቦጋለ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሲያግድበት የተመለሰውን ኳስ አብዱልራህማን መሐመድ በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሮታል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ ወደ ማጥቃት የገቡት ምዓም አናብስቶች አጋማሹ ሳይጠናቀቅ አቻ ለመሆን አደገኛ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፤ በተለይም 43ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ፍሬዘር ካሳ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ከግቡ ርቆ ያለፈባቸው ሙከራ አቻ ሊያደርጋቸው የቀረበ ነበር። አዞዎቹም የአጋማሹ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ይገዙ ቦጋለ ያመከነው አስቆጪው አጋጣሚ መሪነታቸውን ከፍ አድርገው ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ ሊያስችላቸው የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀሙበት ቀርተው ለዕረፍት ወጥተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ምዓም አናብስቶች ተጠናክረው በመመለስ የአቻነት ግብ አግኝተው ወደ ጨዋታ ለመመለስ በሙሉ ኃይላቸው ጥቃት እየፈፀሙ የጨዋታ ብልጫም መውሰድ ችለው የነበረ ቢሆንም ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት ወደ ኋላ አፈግፍገው መከላከሉ ላይ የተጠመዱትን የአዞዎችን ተከላካዮ አልፈው ግብ ለማስቆጠር አልተቻላቸውም። ከተደጋጋሚ ሙከራ በኋላም 56ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዩሐንስ ከርቀት መትቶ ግብ ጠባቂው ጨርፎ ያወጣባቸው አጋጣሚ አቻ ሊያደረጋቸው የቀረበ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።
በአንዷ ግብ ነጥብ ይዘው ለመውጣት ሙሉ ለሙሉ ሲከላከሉ የነበሩት አዞዎቹ በመልሶ ማጥቃት ለመግበት ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ተጨማሪ ግብ አግኝተዋል። ኤፍሬም ታምራት ከሳጥን ውጪ ያሻገረውን ኳስ በአስገዳጅ ቅያሪ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አምበሉ አሸናፊ ፊዳ 88ኛው ደቂቃ ላይ በግንባሩ ጨርፎ መረብ ላይ በማሳረፍ ጨዋታው 2ለ0 በሆነ ውጤት እንዲጠናቀቅ አድርጓል።

