30ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጠናቀቃል፤ ጨዋታዎቹ የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል

ፋሲል ከነማ ከ ባህርዳር ከተማ
በአርባ ሦስት ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት ይበልጥ የሚያስጠጋቸውን ድል ለማግኘት ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በሀያ ሰባተኛው ሳምንት በታምራት ኢያሱ ብቸኛ ግብ ወላይታ ድቻን አንድ ለባዶ ከረቱ በኋላ ድል ማድረግ ያልቻሉት ዐፄዎቹ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ነጥብ ማሳካት አልቻሉም። ሦስት ሦስት ሽንፈትና የአቻ ውጤቶች በእኩሌታ በማስመዝገብ ውጤት አልባ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ሁለት ተከታታይ ድሎች አስመዝግቦ ደረጃውን ማሻሻል የቻለው ቡድኑ ከሁለት ጨዋታዎች መልስ ድል ማድረግ ከቻለ ነጥቡን አርባ ስድስት አድርሶ መሪውን በመከተል የሚገኙ ቡድኖችን ለመጠጋት ያስችለዋል። ይህ እንዲሆን ግን ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወታቸው በብዙ ረገድ መሻሻል ይጠበቅበታል።
በሰላሣ ሰባት ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህርዳር ከተማዎች ሁለት ደረጃዎች ለማሻሻል የሚያስችላቸውን ድል ለማግኘት ዐፄዎቹን ይገጥማሉ።
ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሁለት የአቻ ውጤቶች እና አንድ ሽንፈት በማስመዝገብ ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች ሁለቱን ብቻ ያሳኩት የጣና ሞገዶቹ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባሉ። በውድድር ዓመት በርካታ የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ከሸገር ከተማ ጋር በጣምራ በቀዳሚነት የተቀመጡት ባህርዳሮች በቅርብ ጨዋታዎች በግለ ሰባዊ ስህተቶች ነጥቦችን ለመጣል ተገደዋል። በተከታታይ ሁለት መርሐ ግብሮች ሁለት የጨዋታን መልክ የቀየሩ ግለ ሰባዊ ስህተቶች የተስተዋሉበት ቡድኑ በቀጣይ መሰል ክፍተቶችን ጨምሮ የማጥቃት አጨዋወቱን ይበልጥን ማጠናከር ይጠበቅበታል።
ዐፄዎቹ አብዱላዚዝ አማን እና ብሩክ አማኑኤልን ከጉዳት መልስ ሲያገኙ ሀብታሙ ተከስተ በጉዳት ምክንያት አይኖርም። ባህር ዳር ከተማ ማንያዘዋል ካሳን በጉዳት ሲያጣ የወንድወሰን በለጠ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ 13 ያክል ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን 9 ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ሲፈፅሙ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ሁለት ሁለት ጊዜ ባለድል መሆን ችለዋል። በጨዋታዎቹ ዐፄዎቹ 9 ግቦች እንዲሁም የጣና ሞገዶቹ ደግሞ 6 ጎሎችን አስቆጥረዋል።
ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ መድን
በሀምሳ አምስት ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች ከተከታያቸው ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማስፋት ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በመጨረሻው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ተጋርተው መውጣት የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች በ2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው መቻል ነጥብ መጣሉን ተከትሎ የነጥብ ልዩነቱን ዳግም ወደ አስር ከፍ ለማድረግ ወደ ጨዋታው የሚቀርቡ ይሆናል። በ28ኛው ሳምንት መርሐ ግብር ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻለው ቡድኑ ወሳኙን አጥቂ አቤል ያለው ባልተሰለፈበት ጨዋታ ላይ የተስተዋሉበትን የግብ ማስቆጠር ውስንነቶች መቅረፍ ቀዳሚ ስራው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በሰላሣ አራት ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ መድኖች እስከ ሦስት ደረጃዎች ለማሻሻል የሚያስችላቸውን ድል ለማግኘት የሊጉን መሪ ይገጥማሉ።
ከሦስት የአቻና አንድ ሽንፈት በኋላ ሀዋሳ ከተማን ከመመራት አገግመው በመርታት ዳግም ወደ ድል ተመልሰው ከወራጅ ቀጠናው ፈቀቅ ማለት የቻሉት ኢትዮጵያ መድኖች የዛሬው ጨዋታ ከአደገኛው ቀጠና ይበልጥ የሚርቁበትን ነጥብ ለማግኘት የሚያደርጉት እንደመሆኑ ወሳኝነቱ ትልቅ ነው። በቅርብ ሳምንታት በአወንታነቱ የሚጠቀስና ከመመራት አገግሞ ነጥብ የማግኘት ጥንካሬ የተላበሰው ቡድኑ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ እያደረገ ያለውን ጉዞ ለማሳለጥ የተጋጣሚውን ጠንካራ የፊት መስመር እንቅስቃሴ መግታት ይጠበቅበታል።
በሲዳማ ቡና በኩል ደግፌ ዓለሙ እና መስፍን ታፈሰ ከጉዳት ሲያገግሙ አቤል ያለውም ከቅጣት ይመለሳል። በመድን በኩል ንጋቱ ገብረሥላሴ እና አማኑኤል ኤርቦ በቅጣት በረከት ካሌብ ደግሞ በጉዳት ምክንያት የማይኖሩ ሲሆን የዋንጫ ቱት መሰለፍ አጠራጣሪ ነው።
ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም በሊጉ 13 ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 5 ጊዜ ሲያሸንፍ 6 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀው ኢትዮጵያ መድን ደግሞ 2 ጨዋታ አሸንፏል። በጨዋታዎቹ ኢትዮጵያ መድን 12 ግቦች ፣ ሲዳማ ቡና ደግሞ 10 ግቦችን አስቆጥረዋል።
ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ነጌሌ አርሲ
በሰላሣ አምስት ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወልዋሎዎች እስከ ደረጃዎች የሚያሻሽሉበት ዕድል ለማመቻቸት ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ።
በሁለተኛው ዙር ተሻሽለው በመቅረብ ደረጃቸውን ማሻሻል የቻሉት ቢጫዎቹ በሁለተኛው መንፈቅ ካደረጓቸው አስር ጨዋታዎች ውስጥ በአምስቱ ድል አድርገው ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ችለዋል። በወላይታ ድቻ እና በመቐለ 70 እንደርታ ከደረሰባቸው ሽንፈት በኋላ ባደረጓቸው ሁለት የሊግ እና አንድ የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ድል ማድረግ የቻሉት ወልዋሎዎች በተለይም በቅርብ ሳምንታት በማጥቃት ክፍላቸው የታየው መሻሻል ቀዳሚው ጠንካራ ጎናቸው ነው። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ማስቆጠር የቻለው የአጥቂ ክፍላቸው ጥንካሬ ማስቀጠል እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡናን ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ በተከላካይ ክፍላቸው የተስተዋለው የትኩረት ማነስ መቅረፍም ከቢጫዎቹ ይጠበቃል።
በአርባ አምስት ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ነጌሌ አርሲዎች በ2ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው መቻል ጋር በነጥብ ለመስተካከል ድልን እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በሀያ አምስተኛው ሳምንት አዳማ ከተማን ሁለት ለአንድ ካሸነፉ ወዲህ ላለፉት አምስት ጨዋታዎች ከድል ጋር የተራራቁት ነጌሌ አርሲዎች ከናፈቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ በጥሩ ወቅታዊ አቋም ጋር ከሚገኙ ወልዋሎዎች ይፋለማሉ። በመጨረሻዎቹ አራት የሊግ ጨዋታዎች በመደዳ ነጥብ ተጋርተው በመውጣት ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥብ አራቱን ብቻ ያሳኩት ሰጎኖቹ በሁለተኛው ዙር በብዙ ረገድ ተዳክመዋል። በሁለተኛው መንፈቅ በተደረጉ አስር ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ ያስመዘገበው ቡድኑ ወደ ቀድሞ ብቃቱ ተመልሶ በደረጃ ሰንጠረዡ የላይኛው ክፍል በሚገኘው ፉክክር ለመዝለቅ የማጥቃት ክፍሉን ይበልጥ ማጠናከር ይጠበቅበታል።
በወልዋሎዎች በኩል ብሩክ እንዳለ በጉዳት አምበሉ ፍሬው ሰለሞን ደግሞ በቅጣት ምክንያት አይሰለፉም። በነጌሌ አርሲዎች በኩል አለኝታ ማርቆስ በቅጣት ምክንያት አይሰለፍም፤ ተከላካዩ ዴሲሬ ፓስካልም ከጉዳት አገግሞ ልምምድ ቢጀምርም የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው።
ሁለቱም ቡድኖች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ጨዋታ ነጌሌ አርሲ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።

