በአዲስ አበባ የተደረገው ብቸኛ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል

ሁለት ከሽንፈት የተመለሱ ቡድኖችን ያገናኘው ጨዋታ በጥሩ ፉክክር ጅማሮውን ሲያደርግ ሐይቆቹም አንፃራዊ ብልጫ የወሰዱበት ነበር። ሆኖም ቡድኖቹ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ ጥራት በጎደላቸው እንቅስቃሴዎች ግብ ማግኘት አልቻሉም።
የተሻለ ብልጫ የነበራቸው ሐይቆቹ እስራኤል እሸቱ ከሳጥን ውጪ መቶ የግቡ ቋሚ በመለሰበት ለግብ የቀረበ ሙከራ ቀዳሚ ለመሆን የተቃረቡበት አጋጣሚ እንዲሁም አብነት ደምሴ አሻግሮት ሳጥን ውስጥ የነበረው ተባረክ ሔፋሞ ሞክሮት
ግብ ጠባቂው ፂዮን መርዕድ እና የግቡ አግዳሚ ተጋግዘው ያወጡት ሌላኛው ሙከራም ሐይቆቹን መሪ ሊያደርግ የቀረበ አጋጣሚ ነበር።
በአዞዎቹ በኩልም ኤፍሬም ታምራት አክርሮ በመምታት ያደረገው ሙከራ እና አሸናፊ ፊዳ በሁለት አጋጣሚዎች በግንባሩ ገጭቶ ያደረጋቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።

ጥቂት የማይባሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች የተደረጉበት ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች አደገኛ ሙከራዎችን ያደረጉበት ነበር።
በተለይም በሀዋሳ ከተማ በኩል ጌታነህ ከበደ ከቆመ ኳስ በቀጥታ መቶ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት እንዲሁም ተቀይሮ የገባው አድናን ረሻድ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው እና ቋሚ ብረቱ የመለሰው ሁለት እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ሀዋሳ ከተማን ቀዳሚ ለማድረግ የተቃረቡ ነበሩ። አዞዎቹም ከተደጋጋሚ ሙከራ በኋላ ሰይድ ሀብታሙ በሰራው ስህተት መነሻነት ጎሉን ለቆ መውጣቱን የተመለከተው በፍቅር ግዛቸው መቶት ቋሚውን ታኮ የወጣው አስቆጪው አጋጣሚ ይጠቀሳል። ጨዋታውም ግብ ሳይቆጠርበት 0 ለ 0 ተቋጭቷል።

