መረጃዎች | የ34ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

መረጃዎች | የ34ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

የ34ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሁለተኛ ቀን ዛሬ ቀጥሎ በሚደረጉ አራት ጨዋታዎች ይቀጥላል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

አርባ ሁለት ነጥቦችን በመሰብሰብ አስራ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ንግድ ባንኮች ደረጃቸውን ለማሻሻል ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ይፋለማሉ። በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ሁለት አሸንፎ በሁለት ሽንፈት እና በሁለት አቻ የተለያየው ቡድኑ በተለይም ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን በማሸነፍ ዳግም ወደ አሸናፊነት ተመልሶ የነበረ ቢሆንም በቀጣይ ጨዋታ በመድን ተሽንፏል። 32ኛው ሳምንት ላይ እንዲሁ ሸገር ከተማን በማሸነፍ ወደ ድል መመለስ የቻለ ቢሆንም ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ስለተጋራ አስተማማኝ ደረጃ ላይ ባለመቀመጡ የዛሬውን ጨዋታ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ መግባት ይኖርበታል።

አርባ ስድስት ነጥቦችን ሰብስበው አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ወደ መሪዎች ይበልጥ ለመጠጋት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ይገጥማል። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች አንድ ጨዋታ ብቻ ያሸነፈ ሲሆን ተደጋጋሚ ሽንፈቶችንም በማስተናገድ ሳይጠበቅ ከዋንጫ ፉክክር እየወጣ ይገኛል። ፋሲል ከነማን 3ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፎ ወደ አሸናፊነት ተመልሶ የነበረው ቡድኑ በወልዋሎ ተሸንፎ የአሸናፊነት መንፈሱን ያጣ ሲሆን በ33ኛው ጨዋታ ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋርም ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። ግብ ማስቆጠር የተሳነው ቡድኑ የዋንጫ ፉክክር ውስጥ መቆየት የሚፈልግ ከሆነ የፊት መስመሩን አጠናክሮ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ግድ ይለዋል። ሆኖም ግን ተጋጣሚው ያለበት ደረጃም አስጊ ከመሆኑ አንፃር ጨዋታው ጠንካራ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ቡድኖች በሊጉ ደረጃ 17 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንከሰ 4 ጨዋታወችን ሲያሸንፍ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 5 ጨዋታ ማሸነፍ ሲችል ስምንት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነታቸው 39 ግቦች የተቆጠሩ ሲሆን ባንክ 20 ግቦችን ኤሌክትሪክ ደግሞ 19 ግቦችን መረብ ላይ አሳርፈዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያጣው ተጫዋች የለም። ኢትዮ ኤሌክትሪክም በተመሳሳይ በጉዳት ሆነ በቅጣት ነፃ ሆኖ የዛሬውን ጨዋታ ያደርጋል።

ወላይታ ዲቻ ከ ነጌሌ አርሲ

በአርባ ሦስት ነጥብ አስረኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የጦና ንቦች ከፍ ብለው ለመቀመጥ ሰጎኖቹን ያገኛሉ። ቡድኑ በፋሲል ከነማ ጋር ሽንፈት ካስተናገደ በኋላ ባለፉት ስድስት ሳምንታት ምንም ሽንፈት ያልቀመሰ ሲሆን ማግኘት ካለበት ከ18 ነጥብ ሦስት ጨዋታ በማሸነፍ በሦስቱ አቻ ወጥቶ አስራ አስራ ሁለት ነጥብ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ማግኘቱ ጠንካራ አቋም ላይ መሆኑን ያሳያል። በመከላከሉም ሆነ በማጥቃት አይምሬ የሆኑ እነ መሳይ ሰለሞን እና ያሬድ ዳርዛን የመሳሰሉ ፈጣን አጥቂዎችን የያዘው ቡድኑ የቴዎድሮስ ታፈሰ ወደ አቋሙ ተመልሶ በተከታታይ ጨዋታዎች ፍፁም ያለቁ ኳሶችን ለአጥቂዎች እያቃበለ የመሃል ሜዳውን በሚገባ ተቆጣጥሮ የመጫወት አቅም ያለው ቡድን እንዲሆን አድርጎታል። ባለፉት ስድስት ጨዋታዎችን ባለመሸነፉ ቡድኑ የማሸነፍ ስነልቦና ላይ እንደሚገኝ የሚያሳይ ቢሆንም በመጨረሻዎቹ ሁለት ሳምንታት አቻ ስለተለያየ አሸንፎ ወደ ድል ለመመለስ በማሸነፍ ወኔ ወደ ሜዳ መግባት ይጠበቅበታል።

ሦስተኛ ደረጃን በአምሳ ሁለት ነጥብ ይዞው የተቀመጡት ነጌሌ አርሲዎች ወላይታ ድቻን ይገጥማሉ። ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ ወልዋሎ ዓ/ዩ እና ድሬዳዋ ከተማን በማሸነፍ ወደ ድል መመለስ የቻለ ሲሆን 32ኛው ሳምንት ላይ አሰቃቂ ሽንፈት በመቻል አስተናግዶ በመጨረሻ ሳምንት ከሽረ ጋር ባደረገው ጨዋታ አቻ ተለያይቶ ዳግም ወደ ድል የሚመለስበትን እና ከመሪው ቡድን ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ የሚችልበትን ሰፊ እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በዳዊት ተፈራ ጨዋታ መሪነት የሚታወቀው ቡድኑ ከመቻል ጋር ባለባቸው ጨዋታ ላይ ጉዳት አስተናግዶ በመውጣቱ ለዛ ሽንፈት መዳረጉን እና ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት የተጫዋቹ አለመኖር ቡድኑን ደካማ እንዳደረገው በሚገባ ተመልክተናል። እንዲሁም ጠንካራውን ተከላካይ ሮቦት ሰላሎን ቡድኑ በቅጣት ማጣቱ የሚታወስ ሲሆን ሁለቱ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ የማይመለሱ ከሆነ በተከላካይ መስመር እና መሃል ሜዳ መቸገራቸው አይቀርም። ሆኖም ግን የጨዋታ ስልቱን ቀይረው ፈጣን የመስመር አጥቂዎች ስላላቸው በመስመሮች እየገቡ ግቦችን ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።

በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጀመሪያ ዙር ተገናኝተው ነጥብ ተጋርተው የወጡ ሲሆን አንድ አንድ ግቦችንም አስቆጥረዋል።

ምድረገነት ሽረ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

ሠላሳ ሰባት ነጥቦችን በመሰብሰብ አስራ ሰባተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሽረዎች ከወራጅ ቀጠናው ፈቀቅ ለማለት ሀዲያ ሆሳዕናን ይገጥማሉ። በአዳማ ከተማ አራት ለምንም ተሸንፎ በቀጣዩ ሳምንት ጠንካራውን ኢትዮጵያ ቡና የረታው ቡድኑ ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት የዋንጫ ፉክክር ላይ ከሚገኘውን ከነጌሌ አርሲ ጋር ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ ቡድኑ ከፍተኛ መነሳሳት ላይ እንዲገኝ አድርጎታል። ምንም እንኳን በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ከተቀመጡ ቡድኖች ተረት ቢሰለፍም ከፍ ብለው ከተቀመጡ ቡድኖች ጋር ሲገናኝ ጠንካራ ፉክክር የሚያደርገው ቡድኑ ዛሬ ነብሮቹን የሚያሸንፍ ከሆነ ሙሉ ለሙሉ ከወራጅ ቀጠና ስለሚወጣ ያለበትን ክፍተት ቀርፎ በአሸናፊነት መንፈስ መግባት ይጠበቅበታል። የነ ሽመክት ጉግሳ ከቅጣት መመለስ ተጨማሪ መነሳሳት የፈጠረለት የሚመስለው ቡድኑ የፊት መስመር ላይ ግብ ማስቆጠር ያቆሙትን የነ ዳዊት ዳርጌን ግቦች የሚፈልግበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

አርባ ሁለት ነጥቦችን በመያዝ በግብ ክፍያ አስራ ሦስተኛ ላይ የተቀመጡት ነብሮቹ በወራጅ ቀጠና ስጋት ውስጥ የሚገኘውን ሽረን ይገጥማሉ። ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ በወላይታ ድቻ ሽንፈት አስተናግዶ በሁለት ተከታታይ ሳምንታት ሀዋሳ ከተማን እና የሊጉን መሪ ሲዳማ ቡናን በማሸነፍ ዳግም ወደ ድል መመለስ የቻለ ሲሆን በመጨረሻ ሳምንት ከንግድ ባንክ ጋር ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ ይታወሳል። በማሸነፍ ስነልቦና ላይ የሚገኘው ቡድኑ ባለፉት ስድስት ሳምንታት በአንድ ጨዋታ ብቻ መሸነፉ የተከላካይ መስመሩ ጥንካሬን ያሳያል። ሆኖም ግን በጨዋታዎቹ ከአንድ በላይ ግብ ማስቆጠር የተሳነው የፊት መስመሩ ተጨማሪ ግብ የማስቆጠር የቤት ስራውን መስራት እና ከዛ በላይ ግቦችን ማስቆጠር ይጠበቅበታል። ዛሬ የሚያገኘው ቡድንም ወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኝ ከመሆኑ አኳያ ቀላል ጨዋታ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም።

በሊጉ 4 ጊዜ የተገናኙት ቡድኖቹ ሁለት ጊዜ አቻ ሲለያዩ በቀሪዎቹ ሁለት ግንኙነት ነብሮቹ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን ሰባት ግቦች ሲቆጠሩ ሽረዎች 2 ግቦችን ሆሳዕናዎች በበኩላቸው 5 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ፋሲል ከነማ ከ ሸገር ከተማ

ስምንተኛ ደረጃን በአርባ ስድስት ነጥብ የያዙት ዐፄዎቹ ከሽንፈት ማግስት ሸገር ከተማን ይገጥማሉ። በባህር ዳር ከተማ እና በኢትዮ ኤሌክትሪክ በተከታታይ ከተሸነፈ በኋላ 32ኛው ሳምንት ላይ አዳማ ከተማን 3ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሰው ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት ዳግም በኢትዮጵያ ቡና መሸነፉ ወጥ አቋም ላይ እንደማይገኝ ማሳይ ነው። ከአንድ በላይ ግቦች ተቆጥሮበት ለሽንፈት መዳረጉ ተከላካይ መስመሩ እንደሳሳ ማሳያም ተደርጎ ይወሰዳል። እንዲሁም የፊት መስመራቸው አዳማ ላይ ካስቆጠሩ ሶስት ግብ በጥሩ የሚነሳ ቢሆንም ከመቐለ ጋር የተሸነፉበት ጨዋታ እንዲሁም ከደርቢያቸው ጋርም ግብ ሳያስቆጥር የወጣ በመሆኑ አጥቂዎቻቸው ወደ ግብ ማስቆጠር እንዲመጡ ማድረግ ይጠበቅበታል። ትናንት ቅዱስ ጊዮርጊስ በማሸነፉ ደረጃውን የለቀቀው ቡድኑ ሳይጠበቅ ከዋንጫ ተፎካካሪነት እየወጣ መሆኑ ግልፅ ነው። ስለሆነም ቢያንስ ከመሪዎቹ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ክፍተቶቻቸው ላይ ሰርተው ለማሸነፍ ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አርባ ነጥቦችን በመሰብሰብ በግብ ክፍያ ወልዋሎን በልጠው አስራ አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሸገሮች ከሽንፈት ለማገገም ዐፄዎቹን ይገጥማሉ። ሲዳማ ቡናን በጠባብ ውጤት በማሸነፍ ወደ ተመልሶ በተከታይ ጨዋታዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በመቐለ 70 እንደርታ የተሸነፈው ቡድኑ አሁንም ከወራጅ ቀጠና ስጋት የራቀ ደረጃ ላይ አይገኝም። በሊጉ ልምድ ያላቸውን ከሳጥን ውጪ ግብ ማስቆጠር የሚችሉ አጥቂዎችን የቻለው ቡድኑ ግብ ማስቆጠር ላይ የጎላ ችግር ባይታይበትም ባሳለፍየው ጨዋታ ሳምንታት ግን ይሄንን ጥንካሬ ማጣቱ ለሽንፈት ዳርጎታል። በተለይም የቢኒያም ፍቅሩ ጉዳት አስተናግዶ መውጣቱን ተከትሎ ለዛሬው ጨዋታ የማይደርስ በመሆኑ በሌላ አማራጭ ወደ ሜዳ መግባት ይኖርበታል። ተጋጣሚውም ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት ሽንፈት አስተናግዶ የመጣ ቡድን በመሆኑ የዛሬው ጨዋታ ከባድ የሚያደርግበት ሲሆን ደረጃቸውን ለማሻሻል እንዲሁም ከተሸነፉ ደረጃቸው ዝቅ ማለቱ ስለማይቀር ማሸነፍ ግድ ይላቸዋል።

ቡድኖቹ ከዚህ በፊት በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተው ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

በፋሲል ከነማ በኩል አሚር ሙደሲር በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት እንዲሁም ያሬድ ብርሃኑ በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው። በሸገር ከተማ በኩል ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ጉዳት ያስተናገደው ቢኒያም ፍቅሩ ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ሆኗል።