ሪፖርት | ጦሩ ዳግም ወደ ድል ተመልሷል

ሪፖርት | ጦሩ ዳግም ወደ ድል ተመልሷል

መቻል ኢትዮጵያ መድንን በመሐመድ አበራ ብቸኛ ግብ ሲያሸንፍ የምድረገነት ሽረ እና የፈረሰኞቹ ጨዋታ መብራት በመጥፋቱ ምክንያት ተቋርጧል።

መቻል ከ ኢትዮ መድን

መቻልን ከመድን ያገናኘው ቀዳሚው ጨዋታ በመቻል በላይነት ጅማሮውን በማድረግ በርከት ያሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አስመልክቶናል። በተለይም በሁለት አጋጣሚዎች ቸርነት ጉግሳ ሳይጠቀም የቀረባቸው አስቆጪ ሙከራዎች ሲታወሱ ቻርለስ ሙሴጌ የመታውን ኳስ አቡበከር ኑራ ከጨረፈበት በኋላ ሳጥን ውስጥ ብቻውን አግኝቶ ጠንካራ ያልሆነ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው የተቆጣጠረበት እና ከርቀት የተደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሲመለሳት ቸርነት ጉግሳ ብቻውን አግኝቶ ወደ ላይ የሰቀለበት አስቆጪው አጋጣሚ መቻሎች ቀዳሚ ለመሆን የቀረቡባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።

የጨዋታ ብልጫ የተወሰደባቸው እና ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ ደካማ የነበሩት መድኖች በአጋማሹ ሳሙኤል ሳሊሶ ከመስመር አሻግሮት ወገኔ ገዛኸኝ ወደ ግብ መትቶ ኢላማውን ሳይጠብቅለት ከቀረው ሙከራ ውጪ ሌላ የጠራ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሳይፈጥሩ አጋማሹ ተገባዶ ለእረፍት ወጥተዋል።

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እያስመለከተን በተመለሰው በሁለተኛው አጋማሽ መድኖች ተሻሽለው ቀርበው የተጋጣሚው ሳጥን ደርሰው አስቆጪ አጋጣሚዎችን ከፈጠሩ በኋላ ሳይጠበቅ ግብ አስተናግደዋል። ጨዋታው 61ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ዮዳሄ ዳዊት ከማዕዘን ምት አከባቢ ያሻማውን ኳስ መሐመድ አበራ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብነት ቀይሮ መቻሎችን መሪ አድርጓቸዋል።

ኢትዮጵያ መድን ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ጫና ሲፈጥሩ እያስተዋልን ጨዋታ ሲቀጥል መቻሎችም ተጨማሪ ግብ ለማግኘት በፈጣን ሽግግር የግብ ማግባት ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በተለየም ዳዊት ማሞ የቆመ ኳስ ቀጥታ ወደግብ መትቶት አቡበከር ኑራ ጨርፎ ያወጣባቸው አደገኛው ሙከራ እንዲሁም ታማም ሀቢብ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው የመለሰበት ሙከራ ሲታወስ ጨዋታውም በመሐመድ አበራ ብቸኛ ግብ ለመቻሎች ሦስት ነጥብ በማስገኘት ተቋጭቷል።

ሽረ ከፈረሰኞቹ እያደረጉት የነበረው ሁለተኛው ጨዋታ ያለግብ እስከ 90ኛው ደቂቃ ዘልቆ የነበረ ቢሆንም የሜዳው መብራት በመጥፋቱ ጨዋታው ተቋርጧል። በጨዋታው የተጨመሩት 6 ደቂቃዎችም ነገ 4 ሰዓት የሚደረጉ ይሆናል።